ከፍተኛ ሊግ | የሁለተኛ ቀን ውሎ

ሻሸመኔ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን ከደጋፊዎቹ ጋር በደስታ ባከበረበት ጨዋታ ሲረታ ገላን ከተማ እና ወልዲያ ከተማ በበኩላቸው ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።

\"\"

ምድብ ሀ

በምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ ወልዲያ ከተማ ዱራሜ ከተማን ተገናኝተው አሁንም በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኘው ወልዲያ ድል አድርጓል። የወልዲያን የማሸነፊያ ግቦች በድሩ ኑርሁሴን እና ቢኒያም ጥዑመልሳን ሲያስቆጥሩ የዱራሜን የማስተዛዘኛ ግብ ካፎ ካስትሮ ከመረብ አገናኝቷል። ወሎ ኮምቦልቻ በበኩሉ በጋሞ ጨንቻ በደሳለኝ አሎ ግብ አንድ ለምንም ተረቷል።


ጅማ አባቡና እና አቃቂ ክፍለ ከተማ ያደረጉት የ8 ሰዓት ጨዋታ ያለግብ ሲጠናቀቅ በዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ የሆነው የባቱ ከተማ እና ቡታጅራ ከተማ መርሐ-ግብርም በተመሳሳይ በአቻ ውጤት ተገባዷል።

ምድብ ለ

ረፋዱን ካፋ ቡናን ከጉለሌ ክፍለ ከተማ ያገናኘው መርሐ-ግብር የጉለሌን የተሻለ ተነሳሽነት አሳይቶን በመጨረሻ ደቂቃ ጎል የመዲናይቱን ክለብ አሸናፊ አድርጎ ከፍፃሜ ደርሷል። ከወራጅ ቀጠናው በይበልጥ ራሳቸው ከፍ ለማድረግ በብርቱ የታገሉት ጉለሌዎች መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተሰጠው ጭማሪ ደቂቃ ላይ ማለትም 90+3 ላይ ተቀይሮ የገባው ናትናኤል ሌሊሳ ከመረብ ያሳረፋት ጎል አሸናፊ አድርጓቸዋል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የጉለሌው ስምዖን ሚና በሁለት ቢጫ ባሳየው ያልተገባ ድርጊት ቀይ ካርድ ተመልክቷል።


ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን በጎል ተንበሽብሾ ሦስት ነጥብ ከጂንካ ከተማ ላይ አሳክቷል። ጨዋታውን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረው ከጅምሩ እስከ ፍፃሜው የዘለቁት ደብረብርሃኖች 44ኛው ደቂቃ ላይ መስፍን ኪዳኔ ከግብ ጠባቂ የደረሰውን የስህተት ኳስ ለየተሻ ግዛው ሰጥቶት አጥቂው ወደ ጎልነት ቀይሯታል። ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስም በኤልያስ ፣ የተሻ እና መስፍን ስልነታቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ደብረብርሃኖች 62ኛ ደቂቃ የተሻ ግዛው የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ከቀኝ ወደ ውስጥ የሰጠውን አማካዩ ኤልያስ ማሞ አስቆጥሮታል። 68ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በጨዋታው የጎላው የተሻ ግዛው የሰጠውን መስፍን ኪዳኔ በግንባር ግብ አድርጎት የቡድኑን ሦስተኛ ጎል አስገኝቷል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ በቀሩበት ሰዓት የተሻ ግዛው ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛ ጎልን ከመረብ አሳርፎ ጨዋታው 4ለ0 ተጠናቋል።


ቀደም ብሎ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን ያረጋገጠው ሻሸመኔ ከተማ በተጋጣሚው ነቀምት ከተማ ሽንፈት አስተናግዷል። ጠንካራ የሜዳ ላይ የመሸናነፍ ፉክክርን ያስተዋልንበት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ ተካሂዶ ነቀምትን አሸናፊ አድርጓል። ከዕረፍት መልስ ፉዐድ መሐመድ ለሻሸመኔ ጎል አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ቢያደርግም በውብሸት ሲሳይ ድንቅ ጎል እና በገመቺስ አማኑኤል ተጨማሪ ግብ ነቀምቶች ሻምፒዮኑን ቡድኑ ሻሸመኔን 2ለ1 ረተዋል።


ምድብ ሐ

የረፋዱ የሶዶ ከተማ እና ሮቤ ከተማ ጨዋታ ያለ ግብ አቻ ተጠናቋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እንቅስቃሴ የተመለከትን ሲሆን በፍቃዱ በጋሻው የሚመራው ሶዶ ከተማ ድንቅ እንቅስቃሴ ማድረግ ሲችሉ በሶፊያን ገለቱ የሚመራው ሮቤ ከተማም ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ባደረጉበት አጋማሽ ግብ ሳይቆጠር በአቻ ውጤት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሶዶ ከተማዎች ተጭነው በመጫወት ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ የሚሞከሩትን የግብ ሙከራ ሮቤ ከተማዎች በግብ ጠባቂያቸው ሲሳይ ባንጫ አማካኝነት ግብ ከመሆን የዳኑ ሲሆን በተጨማሪም ሮቤ ከተማዎች የሚያገኙትን ኳስ በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም በሁለቱም ክለቦች ምንም ግብ ሳይቆጠር በአቻ ውጤት ጨዋታው ተጠናቆ ነጥብ ተጋርተዋል።

ቀጥሎ የተከናወነው የቡራዩ ከተማ እና ኦሜድላ ፍልሚያም አቻ ተጠናቋል። የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ትንቅንቅ እና አልሸነፍ ባይነት የበዛበት ጨዋታ ሲሆን ሁለቱም ክለቦች ጨዋታውን ለማሸነፍ ከፍተኛ የሆነ ጥረት ሲያደርጉ ነበር። ይህንንም ተከትሎ በ20ኛው ደቂቃ ቡራዩ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት በቅዱስ ተስፋዬ አማካኝነት ወደ ግብ በመቀየር ቡራዩ ከተማዎችን መሪ ያደረገ ሲሆን በ37ኛ ደቂቃ ኦሜድላዎች በፈጣን ቅብብል ያገኙትን ኳስ የፊት መስመር አጥቂያቸው ታምራት ኢያሱ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ በግንባር በማስቆጠር አቻ ሲሆኑ አጋማሹም በአቻ ውጤት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።


ሁለተኛው አጋማሽ የኦሜድላዎች የበላይነት የታየበት ሲሆን በዚህም አጨዋወት በ59ኛው ደቂቃ ኦሜድላዎች ያገኙትን ኳስ የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው ታምራት እያሱ ሁለተኛውን ግብ በማስቆጠር ኦሜድላዎችን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ቡራዩ ከተማዎች ብዙም ሳይቆይ በአንድ ደቂቃ ልዩነት በ60ኛው ደቂቃ ያገኙትን ኳስ ከሚል አህመድ ግብ በማስቆጠር አቻ ማድረግ ችለዋል። በጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር በአቻ ውጤት ተጠናቆ ነጥብ ሊጋሩ ችለዋል።

በዚህ ምድብ የተደረገው የመጨረሻ ጨዋታ ግን በመሸናነፍ ተጠናቋል። የገላን ከተማ እና ስልጢ ወራቤ የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታ ጥሩ የሚባልና የገላን ከተማ የበላይነት የታየበት ሲሆን በምንተስኖት መንግስቱ እና በመሀል ክፍላቸው አፍቅሮት ሰለሞን ግሩም የሆነ የኳስ ፍሰት እና በፊት መስመሩ በየነ ባንጃው እና የኋላሸት ፍቃዱ ጥሩ የሚባል የግብ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተውሏል። በስልጢ ወራቤ በኩልም ጥሩ የሚባሉ እንቅስቃሴዎችን ሲያስመለክቱን በ28ኛው ደቂቃ ገላን ከተማዎች ያገኙትን ኳስ ከመስመር በማሻገር በምንተስኖት መንግስቱ አማካኝነት ግብ በማስቆጠር ገላን ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል። አጋማሹም በገላን ከተማ መሪነት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።


ሁለተኛው አጋማሽ ስልጢ ወራቤዎች ግብ ለማስቆጠር የገላን ከተማን የግብ ክልል ሲፈትሹ ተስተውሏል።ገላን ከተማዎች ክፍተቶችን በማግኘት ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ሲደርሱ ተመልክተናል። በ64ኛው ደቂቃ ከጥልቅ በመነሳት ኳስን ይዞ ወደ ግብ የሄደው አማካኙ አፍቅሮት ሰለሞን የገላን ከተማን ሁለተኛ ግብ በማስቆጠር መሪነታቸውን ማጠናከር ሲችሉ በ80ኛው ደቂቃ ላይ በስልጢ ወራቤ በኩል ማቲያስ ኤሊያስ በሰራው ጥፋት ከሜዳ በቀይ ካርድ ተሰናብቷል ። ብዙም ሳይቆይ በ83ኛው ደቂቃ አፍቅሮት ሰለሞን ሶስተኛውን ግብ በማስቆጠር ጨዋታው ሊጠናቀቅ ችሏል። ገላን ከተማም ሶስት ነጥብ ማግኘት ችሏል።

\"\"