የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | የ 26ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ

ዛሬ በተጀመረው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት በድሬዳዋ ከተማ 4-2 የተሸነፈው ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ከሊጉ መውረዱን ሲያረጋግጥ የጊዮርጊስ እና የልደታ ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል።

\"\"

ቅዱስ ጊዮርጊስ 0-0 ልደታ ክ/ከተማ

ረፋድ 4 ሰዓት ላይ በተጀመረው ጨዋታ ቀዝቃዛ የነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን ለመውሰድ ጥሩ ፉክክር ቢደረግበትም የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት ነበር። በልደታዎች በኩል 16ኛው ደቂቃ ላይ ህድዓት ካሱ ከሳጥን ውጪ ሞክራው ግብ ጠባቂዋ በረከት ዘመድኩን የመለሰችባት በጊዮርጊሶች በኩል 29ኛው ደቂቃ ላይ ዐይናለም ዓለማየሁ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሙከራ አድርጋ ተጨርፎ በግራው ቋሚ በኩል ለጥቂት የወጣባት ኳስ በአጋማሹ የተሻሉ የግብ ዕድሎች ነበሩ።


ከዕረፍት መልስም ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል 53ኛው ደቂቃ ላይ የጊዮርጊሷ ቤዛዊት ደምፀ ከግራ መስመር ያሻገረችላትን ኳስ ያገኘችው ዐይናለም ዓለማየሁ ያደረገችው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ወጥቷል።  ከዚህ ሙከራ በኋላ ልደታዎች የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ሁለት የተሻሉ ሙከራዎችንም ማድረግ ችለዋል። በቅድሚያም 65ኛው ደቂቃ ላይ ህድዓት ካሱ ከግብ ጠባቂዋ ጋር ተገናኝታ ከፍ አድርጋ በመምታት (ቺፕ) ለማስቆጠር ሞክራ ግብ ጠባቂዋ በረከት ዘመድኩን ስታስወጣባት 86ኛው ደቂቃ ላይም ራሷ ህድዓት ካሱ በተመሳሳይ ሂደት ኃይል ጨምራ ያደረገችው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቷል። ጨዋታውም ያለ ግብ ተጠናቋል።

ድሬዳዋ ከተማ 4-2 ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ

9 ሰዓት ላይ በተጀመረው ጨዋታ ለተመልካች ሳቢ የሆነ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተሻሉ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች 15ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረው ነበር። ሥራ ይርዳው ተከላካዮች ጋር ታግላ ሳጥን ውስጥ ያስገባችውን ኳስ ለሊዲያ ጌትነት አመቻችታ ስታቀብል ሊዲያም በቀላሉ አስቆጥራዋለች። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ከወትሮው በተለየ ድንቅ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉት ንፋስ ስልኮች 22ኛው ደቂቃ ላይ ትዕግሥት ዳልጋ ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ባስቆጠረችው ግብ አቻ ሲሆኑ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ደግሞ በሬዱ በቀለ ከሳጥን አጠገብ ባስቆጠረችው ድንቅ ግብ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በሁለቱም በኩል በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ጥሩ እንቅስቃሴ ያስመለከተን አጋማሽ ሌሎች የጠሩ ዕድሎችን ሳያስመለክተን ተገባዷል።


ከዕረፍት መልስ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጥሩ መንቀሳቀስ የቻሉት ድሬዎች 54ኛው ደቂቃ ላይ ሕይወት ዳንኤል ባስቆጠረችው ግብ አቻ ሆነዋል። ከዚህ ግብ መቆጠር በኋላም ድሬዳዋ ከተማዎች ፍጹም የበላይነቱን ሲወስዱ ተጨማሪ ሁለት ግቦችንም አስቆጥረዋል። በቅድሚያም 69ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባችው ታደለች አብርሃም ቡድኗን መሪ ስታደርግ 79ኛው ደቂቃ ላይ ሜላት ደመቀ ከቅጣት ምት ያደረገችውን ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ መልሶባታል። ሆኖም 85ኛው ደቂቃ ላይ ቤዛዊት ንጉሤ ከግብ ጠባቂዋ ከፍ አድርጋ (ቺፕ) አስቆጥራ ጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ 4-2 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ከሊጉ መውረዱን አረጋግጧል።

\"\"