ሪፖርት | ባህርዳር ከተማ ወደ ድል ተመልሷል

የጣና ሞገዶች ከመመራት ተነስተው ኢትዮጵያ ቡናን 3-1 በመርታት ለዋንጫው የሚያደርጉትን ግስጋሴ ቀጥለዋል።

\"\"

መጠነኛ ፉክክር እያስመለከተን የጀመረው ጨዋታ 7ኛው ደቂቃ ላይ ለግብ የቀረበ ሙከራ ተደርጎበታል። ሮቤል ተክለሚካኤል ያቀበለውን ኳስ የቀኙ የሜዳ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘው አንተነህ ተፈራ ያደረገውን ሙከራ በኳሱ አቅጣጫ  የነበረው ግብ ጠባቂው ፋሲል ገ/ሚካኤል መልሶታል። ሆኖም የራሳቸው የግብ ክልል ውስጥ በቁጥር በዝተው እያሳለፉ የነበሩት ባህርዳር ከተማዎች 22ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራቸውን ሲያደርጉ አለልኝ አዘነ ቀምቶ ያመጣውን ኳስ ለፍጹም ጥላሁን አመቻችቶ ሲያቀብል ባገኘው ኳስ አንድ ተከላካይ አታልሎ መቀነስ የቻለው ፍጹምም በግራ እግሩ ያደረገውን ሙከራ የኳሱ ኃይል የለሽነት ተጨምሮበት ግብ ጠባቂው ሕዝቄል ሞራኬ መልሶበታል።


ጨዋታው 23ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግብ ተቆጥሮበታል። ሬድዋን ናስር በቀኝ መስመር ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ የግብ ጠባቂው ፋሲል ገ/ሚካኤል የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ተጨምሮበት ያገኘው መሐመድኑር ናስር በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮት ኢትዮጵያ ቡናን መሪ ሲያደርግ ይህ መሪነታቸው ግን ከስድስት ደቂቃዎች በላይ መቆየት አልቻለም ነበር። 29ኛው ደቂቃ ላይ ባህርዳሮች በጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ በቀኝ መስመር የወሰዱትን ኳስ ፉዐድ ፈረጃ ወደ ውስጥ አሻግሮት አጥቂዎቹ ባይጠቀሙበትም ያንኑ ኳስ ያገኘው የአብሥራ ተስፋዬ ከግራው የሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሆኖ ያሻገረውን ኳስ ሀብታሙ ታደሠ በግሩም ሁኔታ በግንባሩ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎት የጣና ሞገዶቹን አቻ ማድረግ ችሏል።

ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ባስተናገዱበት የግራው የተከላካይ መስመር የተሰለፈውን ገዛኸኝ ደሳለኝ በጉዳት ምክንያት ጭምር በጫላ ተሽታ በመቀየር በመጠኑ የኋላ መስመራቸውን ለማረጋጋት ሙከራ አድርገው የነበሩት ቡናማዎቹ ጫላ ተሽታ በተፈተነበት የመጀመሪያ አጋጣሚም ግብ ለማስተናገድ ተቃርበው ነበር። ተከላካዩን ማለፍ የቻለው ፍራኦል መንግሥቱ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ፍጹም ጥላሁን ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ሳይጠበቀምበት ቀርቷል። አጋማሹም ግቦች ይቆጠሩበት እንጂ ከተጠበቀበት ግለት በተቃራኒው ተቀዛቅዞ ተጠናቋል።


ከዕረፍት መልስ ባህር ዳር ከተማዎች አጋማሹ በተጀመረ በሴኮንዶች ውስጥ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ፉዐድ ፈረጃ በግራ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ ያገኘው አለልኝ አዘነ በግንባሩ የገጨው ኳስ የግብ ጠባቂውን ሕዝቄል ሞራኬ እጅ ጥሶ መረቡ ላይ አርፏል። ሮቤል ተክለሚካኤል በግንባሩ ከገጨው እና ተከላካዩ ፍራኦል መንግሥቱ ከመለሰው ኳስ  የተሻለ የግብ ዕድል ለመፍጠር የተቸገሩት ቡናማዎቹ 61ኛው 62ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስተናገድ እጅግ ተቃርበው ነበር። በቅድሚያም ፉዐድ ፈረጃ በጥሩ ዕይታ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ በግሩም የመጀመሪያ ንክኪ ተቆጣጥሮ ሁለት ተከላካዮች መሸወድ የቻለው ፍጹም ጥላሁን ኃይል በቀላቀለ ሙከራ ወርቃማውን የግብ ዕድል ሳይጠቀምበት ሲቀር በሴኮንዶች ልዩነት ደግሞ የአብሥራ ተስፋዬ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ሀብታሙ ታደሠ ከግብ ጠባቂው ከፍ አድርጎ(ቺፕ) የሞከረው ኳስ በቀኙ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቷል።

አብዱልከሪም ወርቁን ቀይረው በማስገባት የማጥቃት እንቅስቃሴውን በመጠኑ ለማሻሻል የሞከሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች 68ኛው እና 70ኛው ደቂቃ ላይ በጫላ ተሺታ የግንባር ኳሶች የግብ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም እጅግ ደካማ በነበረው የመከላከል ሽግግራቸው ተጨማሪ ግቦችን አለማስተናገዳቸው በመጠኑ ዕድለኛ አድርጓቸዋል። 74ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ታደሠ ከሳጥን ውጪ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ሕዝቄል ሞራኬ የመለሰበት እና ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሀብታሙ ታደሠ እና ፉዐድ ፈረጃ ሳጥን ውሰጥ ያባከኑት ኳስ የሚጠቀስ ነበር።


የሚያገኟቸውን የግብ ዕድሎች ባለመጠቀማቸው ቁጭት ውስጥ ሳይገቡ በተረጋጋ የማጥቃት እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ የተጋጣሚ  የግብ ክልል ውስጥ መድረስ የቻሉት የጣና ሞገዶቹ 85ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን የገደሉበት ግብ አግኝተዋል። ግብ ጠባቂው ሕዝቄል ሞራኬ ተቀይሮ የገባው አደም አባስ ላይ በሠራው ጥፋት የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት አምበሉ ያሬድ ባዬህ በተረጋጋ አመታት መረቡ ላይ አሳርፎታል። ጨዋታውም በባህር ዳር ከተማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የባህርዳር ከተማው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ኢትዮጵያ ቡና እየተሻሻለ የመጣ ቡድን ከመሆኑ አንጻር ጨዋታው ጠንካራ እንደነበር ገልጸው ቡድኑ እየሄደበት ያለው መንገድ ጤናማ እንደሆነ እና ተጫዋቾቹ  ከፍ ባለ ስነልቦና የቻሉትን ሁሉ አድርገው በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱም የተሻሉ እንደነበሩ ሲጠቁሙ \”ታላቁን ኢትዮጵያ ቡና አሸንፈናል። ይህም ቀጣይ ከአዳማ ከተማ ጋር ለምናደርገው ጨዋታ ጥሩ መንደርደሪያ ነው። ከመመራት ተነስተን ከአቻ ወደ ድል መመለሳችን ለስነልቦና ጥሩ ነው\” ያሉት አሰልጣኙ ተጫዋቾቹ በነጻነት እንዲጫወቱ ስለ ዋንጫ ለመነጋገር ጊዜው እንዳልሆነ አበክረው በመግለጽ ውጤቱን በሄዱበት ለሚከተሏቸው የክለቡ ደጋፊዎች በስጦታ አበርክተዋል። የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ በበኩላቸው በጨዋታው ደካማ እንደነበሩ እና ያዩት ነገር አዲስ እንደሆነባቸው ሲናገሩ መሃል ተከላካዮች ለረጅም ጊዜ አብረው ቢጫወቱም ዛሬ ልክ እንዳልነበሩ እና 38ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የወጣው የግራ መስመር ተከላካዩ ገዛኸኝ ደሳለኝ ያለ ቦታው እየተጫወተ በመሆኑ ደካማ እንደነበር ጠቅሰው ጉዳት ማስተናገዱ ደግሞ ለመቀየር ምክንያት እንደሆናቸው ሲጠቁሙ \”እንደ ቡድን ሁሉም ቦታ ላይ ጥሩ አልነበርንም።\” ብለዋል።

\"\"