የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 1-2 ቅዱስ ጊዮርጊስ

\”ከትልቅ ቡድን ጋር በቁጥር አንሶ መጫወት በጣም ከባድ ነው።\” አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም


\”በዚህ ጭቃማ ሜዳ ተጫውቶ ማሸነፍ ትልቅ ነገር ነው።\” አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ወላይታ ድቻን ካሸነፈበት እና መሪነቱን ካሰፋበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም

ስለ ጨዋታው…

\”ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር ኳስ ይዘን እያጠቃን ለመጫወት ሞክረናል። አጀማመራችን ጥሩ ነበር ግን ጥሩ በነበርንበት አጋጣሚ ደግሞ በቀይ ካርድ ተጫዋች አጣን ፤ ተጋጣሚያችን የዋንጫ ልምድ ያለው ለብሔራዊ ቡድንም ብዙ ተጫዋቾችን ያስመረጠ ቡድን ነው። ከዚህ ቡድን ጋር ለመጫወት የሚያስችለንን ስልት ነድፈን ነበር የመጣነው ግን ቀይ ካርዱ አበላሽቶብናል። ይህንንም ለማስተካከል ጥረት አድርገናል ነገር ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ የዋንጫ አካሄድ የሚያውቅ ቡድን ነው እኛ ደግሞ ልምድ ያላቸውን ከወጣቶች ቀላቅለን ነው የምንጫወተው ፤ ብዙ አቅም በሚፈልገው ጭቃማ ሜዳ ላይ የምንችለውን ሁሉ አድርገናል።\”

\"\"

ያገኟቸውን የግብ ዕድሎችን ስላለመጠቀማቸው…

\”ግብ ከማስቆጠሩ በተጨማሪ አመቻችቶ ማቀበሉ ላይ መጣደፎች አሉ። አጥቂዎቻችን በሙሉ ወጣቶች ናቸው። የመጫወት ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነው ግን ከልምድ ማነስ አንጻር ሳጥን ውስጥ ተረጋግቶ የመጫወቱ ነገር አሁንም ይቀራል። የአቅማችንን ሁሉ ታግለናል። ከትልቅ ቡድን ጋር በቁጥር አንሶ መጫወት በጣም ከባድ ነው።  ውጤቱንም ተቀብለናል።

አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ

ስለ ጨዋታው…

\”ጨዋታው ከባድ ነበር። ሜዳው ጭቃ ነው ጨዋታውም ጠንካራ ነበር። እነሱ ደግሞ ጉልበት ያላቸው ናቸው ከሞላ ጎደል ጥሩ ጨዋታ ነበር።

ተጋጣሚን ስላገኙበት መንገድ…

ወላይታ ድቻ ተጫዋች ወጥቶበታል ነገር ግን ቡድኑ ጠንካራ ነበር። አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም የሚሠራው ቡድን ጠንካራ ነው። ሆኖም መጫወት ባለብን ዘይቤ መጫወት ብንችል ኖሮ ከዚህም በላይ መጫወት እንችል ነበር። ግብ የተቆጠረብንም ከራሳችን ሰህተት የተነሳ ነው።

\"\"

ከተከታታይ ነጥብ መጣሎች በኋላ ወደ ድል መመለሳቸው በቀጣይ ጨዋታዎች ላይ ስለሚኖረው ሚና…

ትልት አስተዋጽኦ አለው። በዚህ ጭቃ ሜዳ ተጫውቶ ማሸነፍ ትልቅ ነገር ነው። ማሸነፋችንም ለቀጣዩ ጨዋታ በማነቃቃት ትኩረት እንድንሰጥ የሚያደርግ ነው። በቀጣይም መጫወት ባለብን ዘይቤ ከተጫወትን ከዚህ በላይ መንቀሳቀስ እንችላለን እና የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፋችን በጣም ጥሩ ነው።