ሪፖርት | የጦና ንቦቹ ብርትካናማዎቹን በመርታት ከወራጅ ቀጠናው ስጋት በመጠኑ ፈቅ ብለዋል

ወላይታ ድቻ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር በመገናኘት የወራጅነት ስጋቱን በመጠኑ አቃሏል።

\"\"

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በሀዋሳ ከተማ 3ለ1 የተረቱት ወላይታ ድቻዎች በጉዳት ምክንያት ከዛሬው ጨዋታ ውጪ የሆነውን በረከት ወልደዮሐንስ በያሬድ ዳዊት ብቻ ተክተው ወደ ሜዳ ሲገቡ በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት በአዳማ ከተማ 2ለ1 የተሸነፉት ድሬዳዋ ከተማዎች በበኩላቸው ዳንኤል ተሾመ፣ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ፣ አቤል አሰበ እና ሱራፌል ጌታቸውን አሳርፈው ፍሬው ጌታሁን፣ እንየው ካሣሁን፣ ብሩክ ቃልቦሬ እና ቢኒያም ጌታቸውን ወደ አሰላለፍ መልሰው ጨዋታውን ቀርበዋል።


የጨዋታውን የኃይል ሚዛን በኳስ ቁጥጥር ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የጀመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በእርጋታ ኳስን በማንሸራሸር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲጥሩ ታይቷል። በተቃራኒው ቀጥተኛ አጨዋወትን የመረጡት ወላይታ ድቻዎች በበኩላቸው የድሬን የኳስ ቅብብል እያጨናገፉ በፈጣን ሽግግር ግብ ለማስቆጠር ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል። ብዙም የግብ ዕድል ያልተፈጠረበት ጨዋታው እስከ 30ኛው ደቂቃ ድረስ የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ባይደረግበትም ጥሩ የሜዳ ላይ የአልሸነፍ ባይነት ትግል ሲደረግበት ነበር።


እንደገለፅነው በጨዋታው ግማሽ ሰዓት ወላይታ ድቻዎች የጨዋታውን የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገዋል። በዚህም ቢኒያም ፍቅሩ ከቀኝ የሳጥኑ ክፍል ከዘላለም አባቴ የተቀበለውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብ ቢልከውም ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን አምክኖበታል። ወላይታ ድቻዎች ከኳስ ጋር ጊዜ ባያሳልፉም ወደ ግብ በመድረስ ረገድ ከድሬዳዋ ከተማ የተሻለ ነበሩ። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩትም ከቅጣት ምት መነሻን ያደረገ ኳስ ተከላካዮች ገጭተው ሲመልሱት ከሳጥኑ ውጪ የነበረው ቃልኪዳን ዘላለም አግኝቶት በአንድ ንክኪ መሬት አንጥሮ መረብ ላይ አሳርፎት ድቻ መሪ ሆኗል።


ሁለተኛውን አጋማሽ በፈጣን የተጫዋች ለውጥ የጀመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች የመከላከል ባህሪ ያለው አማካይ አስወጥተው የማጥቃት ባህሪ ያለው አጥቂ ወደ ሜዳ አስገብተዋል። አጋማሹ እንደተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃም ውጥናቸው ሰምሮ አቻ ሆነዋል። በዚህም ከግራ መስመር የተሻማውን ኳስ ግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ በሚገባ ማፅዳት ሳይችል ቀርቶ ዳዊት እስጢፋኖስ አግኝቶት ግብ አድርጎት ቡድኑን ወደ ጨዋታው መልሷል።


ጨዋታው 66ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ፍፁም ሌላ መልክ መያዝ ጀምሯል። እስከተጠቀሰው ደቂቃ ድረስ ድሬዳዋዎች የተሻለ ቢንቀሳቀሱም በቁጥር በዝተው የድሬ የግብ ክልል የደረሱት ወላይታ ድቻዎች የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። የግብ ዘቡ ፍሬው የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምትም ቃልኪዳን ዘላለም ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አድርጎታል። ይህቺ የመሪነት ግብ ከተገኘች ከአንድ ደቂቃ በኋላ ደግሞ ዘላለምን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው ዮናታን ወደ ግብ የመታውን ሌላ ኳስ ፍሬው ሲመልሰው ያገኘው ቢኒያም ፍቅሩ የቡድኑ ሦስተኛ ግብ አድርጎት የጨዋታውን ቁጥጥር በአስተማማኝ ሁኔታ ወደ ድቻ አምጥቷል። በቀሪ ደቂቃዎች ድሬዎች ቢያንስ አንድ ነጥብ ለማግኘት ቢያስቡም ሳይሳካላቸው ጨዋታው በድቻ አሸናፊነት ተፈፅሟል።


ከጨዋታው በኋላ የድሬዳዋ ከተማው አሠልጣኝ አስራት አባተ በጨዋታው አንድ እኩል እያሉ ጥሩ ቢንቀሳቀሱም በግብ ጠባቂያቸው ስህተት የተቆጠረባቸው የፍፁም ቅጣት ምት እንዲሁም ወዲያው ሳይረጋጉ የተቆጠረው ጎል ውጤቱን ወደ ድቻ እንደወሰደው አመላክተው በቀጣይ የአርባምንጭ ጨዋታ ውጤት አግኝተው ከአደገኛው ቀጠና እንደሚወጡ ገልፀዋል። ሦስት ነጥብ ያገኙት የወላይታ ድቻው አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በበኩላቸው ጨዋታውን በቁርጠኝነት እና በተራበ ስሜት እንደተጫወቱ ጠቁመው በህይወታቸው እንደ ዛሬ ተደስተው እንደማያውቁ ተናግው ከቡድናቸው ጎን የነበሩትን ደጋፊዎች አመስግነዋል።

\"\"