አዲሶቹ የዋልያዎቹ ተመራጮች ስለመጀመርያው የብሔራዊ ቡድን ጥሪያቸው ምን ይላሉ ?

በዘንድሮ የውድድር ዓመት ጥሩ ብቃት አሳይተው ለመጀመርያ ጊዜ ሀገራቸውን ለመወከል ጥሪ የቀረበላቸውን ሦስት ተጫዋቾች ሀሳብ ትናንት ማቅረባችን የሚታወስ ሲሆን ዛሬ ደግሞ በተመሳሳይ የሁለት ተጫዋቾች ሀሳብ ይዘን ቀርበናል።

አማኑኤል ተርፉ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ስለ ወቅታዊ አቋም…

በግል የውድድር ዓመቱ ሁለት መልክ ነበረው። ጥሩ የሆንኩበት ጊዜ ነበር ፤ በሆነ ጊዜ ደግሞ የአቋም መዋዥቅ አጋጥሞኝ ነበር። በስተመጨረሻ ግን ወደ አቋሜ ተመልሼ ለብሄራዊ ቡድንም መመረጥ ችያለው። በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ።
\"\"
የብሄራዊ ቡድን ጥሪ የፈጠረብህ ስሜት…

ብሄራዊ ቡድን መወከል ትልቅ ነገር ነው። ሀገሪቱ ካሉ ሊጎች 23 ተጫዋቾች ብቻ ናቸው የሚመረጡትና ራስህን እዛ ቦታ ማግኘት ደስ ይላል። ዓመቱን ሙሉ የምትለፋው ለብሄራዊ ቡድን መመረጥ እና ሃገርን ለማገልገል ነው ፤ ለእኔ ጥሩ ጅማሮ ነው ብዬ ነው የማስበው። ብቃቴ ጥሩ ስለነበር እመረጣለው ብዬ ጠብቄ ነበር። ልምድ ያላቸው የቡድን አጋሮቼም በጥሩ ወቅታዊ አቋም እንዳለው ይነግሩኝ ነበር ፤ ብሄራዊ ቡድንም የመመረጥ ዕድል እንዳለኝ ይነግሩኝ ነበር።

በቀጣይነት በብሄራዊ ቡድኑ ለመጫወት ያለው ዝግጁነት…

ይሄ እንደ ጅማሮ ጥሩ ነው። በዚህ ነገር ብቻ ረክቼ ቁጭ አልልም፤ በቀጣይም በክለብ ደረጃም ጠንክሬ በመስራት ያለኝን አቅም አውጥቼ ሀገሬን ማገልገል ነው የምፈልገው።

ቢንያም ገነቱ (ወላይታ ድቻ)

ስለ ውድድር ዓመት አቋሙ…

ውድድር ዓመቱ ጥሩ ነበር። በግሌም ጥሩ ዓመት ነው ያሳለፍኩት ፤ እንደ ቡድንም ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት ነው ያለን። የቡድኑ እንዲ መሆን ነው እንድጎላ ያደረገኝ። ሊጉ ከሌላው ጊዜ በተለየ ጠንከር ብሏል ፤ የቡድኖቹ አቀራረብ መመልከት ትችላለህ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ከጎኔ ጥሩ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች መኖርም ትልቅ አስተዋፅዖ አድርጎልኛል። በግልም ብዙ ነገር እንዳሻሽል ረድተውኛል ፤ በርግጥ አሁንም ከዚህ በላይ ማሻሻል እንዳለብኝ ይሰማኛል። ለዚህም ጠንክሬ እሰራለሁ። በአጠቃላይ ከግል ጥረቴ ባልተናነሰ የቡድን አጋሮቼ ጥሩ መሆን ብዙ ነገር ጠቅሞኛል።

የብሄራዊ ቡድን ጥሪ የፈጠረብህ ስሜት…

በጣም ነው ደስ ያለኝ። ቤት ነበርኩ ፤ መጀመርያ ወንድሜ ነው ደውሎ የነገረኝ። ከዛ በኋላ ደስታው ልዩ ነበር። ሀገርን መወከል ማለት ትልቅ ነገር ነው ፤ ትልቅ ዕድል ነው። ከእኔ በላይ ደግሞ ቤተሰብ ጠብቀውት ስለነበር በጣም ደስ ብሏቸዋል።
\"\"
በቀጣይነት በብሄራዊ ቡድኑ ለመጫወት ያለው ዝግጁነት…

በቀጣይነት ለመመረጥ በጣም ትልቅ ስራ ይጠይቃል። እኔም ይህንን ተገንዝቤ አሁን ካለው ነገር በበለጠ ጠንክሬ በመስራት ሀገሬን በቀጣይነት ማገልገል እፈልጋለሁ። በቡድኑ ካሉት ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች በሜዳም ከሜዳም ውጭ ብዙ ልምድ እየወሰድኩ ነው።

* ለብሄራዊ ቡድን ለመጀመርያ ጊዜ ጥሪ ከደረሳቸው ተጫዋቾች መካከል የባህርዳር ከተማው አጥቂ ሀብታሙ ታደሰን እንደሌሎቹ ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም ፤ ከሀብታሙ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መድኖቹ ብሩክ ሙልጌታ እና ወገኔ ገዛኸኝ በክለቡ የውስጥ መመርያ ደንብ ምክንያት ሀሳባቸውን ማካተት አልቻልንም።