ቆይታ ከነብሮቹ የኋላ ደጀን ፓፔ ሰይዱ ጋር

👉 \”በየሳምንቱ የምጥረው እና የምለፋው ለቡድኔ የተሻለ ውጤት እንዲመጣ ነው\”

👉 \”ኢትዮጵያ በጣም ጥሩ ሀገር ናት። ጥሩ ሕዝቦች ናቸው ያሉት ፤ ሀገሬ እንዳለሁ ነው የሚሰማኝ\”

👉 \”የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችም ይመቹኛል ፤ በተለይ የዲዲ ጋጋ እና የቴዲ አፍሮ ሙዚቃዎች ያዝናኑኛል\”

👉 \”ከሦስት ዓመታት በፊት ይመስለኛል በዚህ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ እንድጫወት ተጠይቄ ነበር። ነገር ግን…\”

👉 \”በክለቤ ጥሩ ተጫዋቾች አሉ ፤ ግን ደግሞ ለእኔ እንደ ቡድን በጣም ጥሩ ቡድን አለን ማለት ይከብደኛል\”

በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ በግብ ጠባቂነት ሚና የውጪ ሀገር ተጫዋቾች ወደ ሀገራችን መምጣት የጀመሩት 1997 ላይ እንደሆነ ይታወቃል። ዩጋንዳዊው ዴኒስ ኦኒያንጎ በቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ የኢትዮጵያን ሊግ ከተዋወቀበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የግብ ዘቦች ወደ ሊጋችን የመጡ ሲሆን በዘንድሮ የውድድር ዓመት በከፍተኛው የሊግ እርከን ውድድር ከተመለከትናቸው አዳዲስ ግብ ጠባቂዎች መካከል የሀዲያ ሆሳዕናው ፓፔ ሰይዱ ንዲያዬ አንዱ ነው።

ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል ያነሱ ግቦችን ያስተናገዱት ነብሮቹ ከዚህ ስኬታቸው ጀርባ ፓፔ ሰይዱ ተጠቃሽ ነው። ተጫዋቹ በ14 የሊጉ ጨዋታዎች ግቡን ባለማስደፈር ጠንካራነቱን እያሳየ የሚገኝ ሲሆን ከአማካዩ ብሩክ ማርቆስ በመቀጠል ብዙ ደቂቃዎችን ሜዳ ላይ ግልጋሎት በመስጠት የቡድኑ ቁልፍ ሰው እንደሆነም እያሳየ ይገኛል።
\"\"
በሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር የተወለደው የ30 ዓመቱ ፓፔ በእድገቱ ትልቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱለት ቤተሰቦቹ ልዩ ፍቅር እንዳለው ይናገራል። እንደ ማንኛውም ታዳጊ በሚኖርበት አካባቢ ከእኩዮቹ ጋር ኳስን በመጫወት የጀመረውን የተጫዋችነት ህይወቱንም ወደ አካዳሚ ገብቶ በትምህርት እንዳጎለበተው በመጥቀስ ከአካዳሚ ጀምሮም ግብ ጠባቂ የመሆን ፍላጎት በዐምሮ ውስጥ እንደነበረ ይገልፃል።

አንድ ሜትር ከዘጠና ስድስት ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው ተጫዋቹ ከልጅነቱ ጀምሮ ታዋቂውን የቀድሞ የቼልሲ ግብ ጠባቂ ፒተር ቼክ እያደነቀ እዚህ ደርሷል። ከ2017 ጀምሮ ሀገሩ ሴኔጋልን በአህጉራዊ እና ቀጠናዊ ውድድሮች እያገለገለ የሚገኘው ተጫዋቹ በዘንድሮ የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ያሳየውን መልካም የሚባል ብቃት በመንተራስ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል።

ወደ ኢትዮጵያ እንዴት ልትመጣ ቻልክ?

ከሦስት ዓመታት በፊት ይመስለኛል በዚህ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ እንድጫወት ተጠይቄ ነበር። ነገር ግን በጊዜው ብዙ ዕድሎች ስለነበሩኝ ነው ያልመጣሁት። ምክንያቱም እዚህ ስላለው ሊግ ምንም አላውቅም ነበር። ወደ አውሮፓ ሄጄ በዴንማርክ ተጫውቼ ከተመለስኩ በኋላ አናግሮኝ የነበረው ሰው ድጋሚ አናገረኝ። በዴንማርክ የምጫወትበት ክለብ የፋይናንስ ችግር አጋጥሞት ነበር። ይህንን ተከትሎ ከክለቡ ስለለቀኩ በሰዓቱ ለመምጣት ነጻ ነበርኩ።

ከዴንማርክ ወደ ኢትዮጵያ ነው በቀጥታ የመጣከው። ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት የወሰንክበት ምክንያት ምንድን ነው? የኢትዮጵያን ሊግስ እንዴት መረጥክ?

በዴንማርክ ሁለተኛ ሊግ የተወሰኑ ጨዋታዎችን አድርጌ ነበር። ከእነዚህ ጨዋታዎች በኋላ ቡድናችን ትልቅ ኪሳራ አጋጠመው። በዚህ ሰዓት ሶፎ እና ኤዶሚያስ የሚባሉ የተጫዋች ወኪሎች \’መምጣት የምትችል ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ እገዛህን የሚፈልግ አንድ ቡድን አለ\’ አሉኝ። እኔም እሺ ችግር የለውም መጥቼ ማየት እችላለሁ አልኩ። ከዚህ በፊት ስለ ሊጉ ምንም ነገር አላውቅም ነበር። ከዛ በኋላ እኔ ፕሮፌሽናል ነኝ ሳልጫዎት መቆየት ለእኔ ጥሩ አይደለም ብዬ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ወሰንኩ። እግር ኳስ ለእኔ ሕይወቴ ነው።

ኢትዮጵያን እንዴት አገኘካት?

ኢትዮጵያ በጣም ጥሩ ሀገር ናት። ጥሩ ሕዝቦች ናቸው ያሉት ፤ ሀገሬ እንዳለሁ ነው የሚሰማኝ።

ሊጉን ቶሎ የለመድክ ይመስላል። እንደ አዲስ ሊግ ለመልመድ ከብዶህ ነበር?

እንዳልኩህ የውድድር ዘመኔን የጀመርኩት (2021/2022) በዴንማርክ ነው። ቡድኔ ወደ ኪሳራ ሲገባ ነው እዚህ የመጣሁት። እኔ ያሰብኩት በቃ ስለ ቀጣይነት ብቻ ነው። ይህንን ሊግ አላውቀውም። ከመጣሁ በኋላ ግን ልምምዶችን እና ኢትዮጵያዊ ተጫዋቾችንም እያየሁ ነገሮችን ለመልመድ ሞክሬያለው። ሁሉንም ነገር ዐይቼ ተረድቻለሁ። በየሳምንቱ የምጥረው እና የምለፋው ለቡድኔ የተሻለ ውጤት እንዲመጣ ነው። በዚህ ሂደት ሊጉን በቶሎ ለምጃለው።

\"\"

ኢትዮጵያዊያንን ግብ ጠባቂዎች እንዴት አገኘካቸው?

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጥሩ ጥሩ ግብ ጠባቂዎችን አይቻለው። ግን እንደሚታወቀው የግብ ጠባቂ ቦታ እጅግ በጣም ከባድ ቦታ ነው። አንዳንድ ጊዜ ስህተቶችን ልትሰራ ትችላለህ። እኔም ለምሳሌ ስህተቶችን እሰራለው። እርግጥ እግርኳስ በአጠቃላይ በስህተት የተሞላ ነው ግን የግብ ጠባቂ ቦታ ደግሞ ከሌሎች ቦታዎች ከፍ ይላል። የሆነው ሆኖ በኢትዮጵያ ጥሩ ጥሩ ግብ ጠባቂዎችን አይቻለው።

በሊጉ ብዙ መረብህን የማታስደፍር ግብ ጠባቂ እንደሆንክ ቁጥሮች ያስረዳሉ። የቡድኑ ጠንካራ የመከላከል አጨዋወት እንዳለ ሆኖ አንተም ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎችን ስታመክን ይታያል። ይህንን ብቃትህን እንዴት አዳበርከው?

ብቃቴን ያሻሻልኩት ሁል ጊዜ ጠንክሬ ስለምሰራ ነው። ጨዋታዎች ላይም ሙሉ ትኩረቴን እንቅስቃሴ ላይ ስለማደርግ ነው። በጨዋታ ላይ እየተዝናናው ነው የምጫወተው። እንዳልኩት ለግብ ጠባቂ ትኩረት ወሳኝ ነው። በአጠቃላይ ግን ተግቶ መስራት አስፈላጊ ነው። ሳምንቱን ሙሉ ጥሩ ልምምድ ከሰራህ እና በዐምሮም ዝግጁ ከሆንክ በሳምንቱ መጨረሻ የጨዋታ ቀን ጥሩ ትሆናለህ።

ወደ ልምምድ ሁል ጊዜ ስሄድ ጥሩ ነገር ለመስራት በጣም ተዘጋጅቼ ነው። እኔ ፕሮፌሽናል ተጫዋች ነኝ። የግብ ጠባቂ አሠልጣኝ ለብቻ ስላለ አሠልጣኙ ያዘዘኝን በሚገባ ነው የምሰራው። አሠልጣኙ ከሚሰጠኝ ነገር ውጪ እኔም ማሳደግ የምፈልገው ነገር ካለ እየጠየኩት እንዲረዳኝ አደርጋለው።

ስለቡድንህ ሀዲያ ሆሳዕና የዘንድሮ ብቃት ምን ትላለህ?

በክለቤ ጥሩ ተጫዋቾች አሉ ፤ ግን ደግሞ ለእኔ እንደ ቡድን በጣም ጥሩ ቡድን አለን ማለት ይከብደኛል። ጥሩ ቡድን ቢኖረን ኖሮ ለዋንጫ እንፎካከር ነበር። ዋንጫ እናገኝ አልያን ሁለተኛ እንወጣ ነበር። የቡድናችን ብቃት ወጥ አይደለም። ዛሬ ጥሩ ከተጫወትን ነገ ላንጫወት እንችላለን። ጥሩ ቡድን ቢኖረን ኖሮ እኔም ዋንጫ አገኝ ነበር።

በእግርኳስ ህይወትህ ያጋጠመህ ጥሩም ይሁን መጥፎ አጋጣሚ ካለ አጋራን እስቲ…?

ትንሽ አስቸጋሪ ነገር በህይወቴ ገጥሞኝ ያውቃል። በሴኔጋል የ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የሚጫወት አንድ ጓደኛ ነበረኝ። ጥሩ ተጫዋች ነበር። ጊዜው 2015 ላይ ነው። ለአፍሪካ ዋንጫም ዝግጅታችንን እያደረግን ነበር። በጊዜው በጥሩ ሁኔታ ልምምዳችንን እየሰራን ነበር። አንድ ቀን ምሽት ላይ ጓደኛዬ ወደእኔ ወደ እኔ ክፍል መጣና ብዙ ነገር አወራኝ። ሰዓቱ ወደ እኩለ ለሊት ሲጠጋ ሁሉም ተጫዋቾች ሲተኙ ይህ ጓደኛዬም ወደ ክፍሉ ሄዶ ተኛ። ጠዋት ላይ ከጓደኛዬ ጋር ክፍል የሚጋራው ሌላ ተጫዋች ወደ እኔ መጥቶ ቀስቅሶኝ ጓደኛችን እንዳልተነሳ ነገረኝ። እኔም ሄጄ ብቀሰቅሰው ሊነሳ አልቻለም ፤ ጓደኛዬ ህይወቱ አልፎ ነበር። ይህ አጋጣሚ ለእኔ በጣም አስቸጋሪ ጊዜ ነበር። እርግጥ ነው ሁሉም ሰው ህይወቱ ያልፋል የእሱ ግን ትንሽ ይከብዳል። ይህንን አጋጣሚ መቼም በህይወቴ አልረሳውም። የሆነው ሆኖ ከ3 ሳምንታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ሄደን ፈጣሪ ይመስገን ውድድሩን ለእርሱ ብለን አሸነፍን። በዚህ ሰዓት ለእርሱ ዋንጫውን በማግኘታችን ደስ ተሰኝተናል። አጋጣሚው ከባድ ቢሆንም ሁላችንም በዐምሮ ረገድ እጅግ ጠንካሮች ሆነን ነው ዋንጫውን ያሳካነው።

ሌሎችም መጥፎ አጋጣሚዎች ይኖራሉ። እነዚህ መጥፎ አጋጣሚዎች ደግሞ እኔን እያጠነከሩኝ ነው የሚሄዱት። በእግርኳስ ህይወት ነገሮች አንዳንዴ ጥሩ አንዳንዴ ደግሞ መጥፎ ይሆናሉ። ስለዚህ መጥፎ ነገሮች ሲከሰቱ ጠንካራ ሆነህ ማለፍ ይጠበቅብሀል።
\"\"
ከጨዋታ በፊት ምን የማድረግ ልማድ አለህ?

ከጨዋታ በፊት ለየት ያለ ነገር አለኝ። ሁል ጊዜ ጨዋታ ላደርግ ወደ ሜዳ ስገባ የማዳምጠው ለየት ያለ ሙዚቃ አለኝ። ይህ ሙዚቃ በጣም እንድነቃቃና በጥሩ ትኩረት ላይ እንድገኝ ያደርገኛል።

የማንን ሙዚቃ ነው የምትሰማው? የኢትዮጵያ ሙዚቃስ…?

ብዙ ጊዜ የሀገሬን ሙዚቃ እሰማለው። በተለይ ኤልሀጂ ዲዩፍ የተባለ ሙዚቀኛ ስራዎችን አዳምጣለው። እንዳልከከው የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችም ይመቹኛል ፤ በተለይ የዲዲ ጋጋ እና የቴዲ አፍሮ ሙዚቃዎች ያዝናኑኛል።