ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሠ በነገው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ከዳኝነት ትሸኛለች

ከሀገር ውስጥ ውድድሮች አልፎ በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች መዳኘት የቻለችው ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሠ በነገው ዕለት በሚደረገው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ከዳኝነት ራሷን እንደምታገል ታውቋል።
\"\"
በጅማ ከተማ የተወለደችው ሊዲያ ታፈሠ ከእግርኳስ በላይ የምትወደውን ቅርጫት ኳስ ለመቀጠል ወደ አዲስ አበባ ብትመጣም የዳኝነቱ ሙያ በልጦባት የፋርማሲ ትምህርቷን እየተማረች ጎን ለጎን የዳኝነት ኮርሶችን በመውሰድ ራሷን አጎልብታለች። በዋናው የሀገራችን የሊግ እርከንም 1997 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የወንዶችን ፕሪምየር ሊግ በረዳት ዳኝነት መርታ ረጅሙን የስኬት ጉዞዋን ተያያዘች። በዓመቱም ኒጀር እና ሊቢያ ያደረጉትን ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ በመምራት የመጀመሪያ የኢንተርናሽናል አልቢትርነትን ህይወቷን \’ሀ\’ ብላ ጀመረች። ከዛም በርካታ አህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ የሀገራት እንዲሁም የክለቦች ጨዋታዎችን እየመራች ያሳለፈች ሲሆን በነገው ዕለት በሚደረገው የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ከዳኝነት እንደምትሸኝ ታውቋል።

በነገው ዕለት በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የሚደረገው ጨዋታ ከመጀመሩ በፊትም የሙያ አጋሮቿ እሷን በክብር ለመሸኘት እንደተሰናዱ ተጠቁሟል።
\"\"
ከነገ በኋላ ሊዲያ በሜዳ ጨዋታዎችን ባትመራም ከካፍ በመጣላት ዕድል የዳኞች ኢንስትራክተር ሆና እንደምትቀጥል ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል። ከሰሞኑ በካይሮ ከዛምቢያዊው ዳኛ ጃኒ ሲካንዝዌ ጋር ስልጠናዋን የወሰደችው ሊዲያ በቀጣይ የሴካፋ ከ18 ዓመት በታች ውድድር በኢንስትራክተርነት የመጀመሪያ ስራዋን እንደምትጀምርም ይጠበቃል።