መረጃዎች | 107ኛ የጨዋታ ቀን

ፕሪሚየር ሊጉ ከብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ በኋላ ሲመለስ የ28ኛው የጨዋታ ሳምንት ማገባደጃ በመሆን የሚደረጉትን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በ 38 ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቡናማዎቹ እና በ 59 ነጥቦች ሊጉን እየመሩ የሚገኙት ፈረሠኞቹ 46ኛውን የሸገር ደርቢ ጨዋታ ነገ 9 ሰዓት ላይ ያደርጋሉ።

በኢትዮጵያ መድን 2ለ1 ከተረቱ በኋላ በብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ምክንያት የ 21 ቀናት ዕረፍት ያገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች በተለይም እያሻሻሉት የመጡትን እንቅስቃሴ ለማስቀጠል ተቸግረው ካለፉት 6 ጨዋታዎች 2 ጊዜ ብቻ ድል ማድረጋቸው የወጥነት ችግር እንዳለባቸው ሲጠቁም ያገኙት የዕረፍት ጊዜ አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ ሀሳባቸውን ለማስረጽ እና ቡድናቸውን ወደ ሚፈለጉት እንቅስቃሴ እንዲመጣ በማድረጉ በኩል በተለይም ከአማኑኤል ዮሐንስ ውጪ ያሉት ቀሪው የቡድን አባላት አንድ ላይ መቆየታቸው ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል። ባለፉት 8 ጨዋታዎች 13 ግቦችን ያስቆጠረው ቡድኑ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የነበረበትን ችግር በመጠኑ ቢቀርፍም በድል ለመታጀብ ግን በቂ አልሆኑለትም። ኢትዮጵያ ቡና በውድድር ዓመቱ ባሳካቸው 9 ድሎች ሁሉ ቀድሞ ግብ አስቆጥሯል። ቡድኑ ቀድሞ ግብ ከተቆጠረበት በኋላ የሚገጥመው የስነ ልቦና ዝቅታ ተጫዋቾቹ ላይ ተጥሎ የነበረውን ከፍተኛ የኃላፊነት ጫና የሚያመላክት ነው። ሆኖም የሜዳሊያው ደረጃ ውስጥ ለመግባት ዕድል የሌለው ቡድኑ ለክብሩ ሲል በነገው ዕለት ከከተማ ተቀናቃኙ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ጠንካራ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
\"\"
ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኙት እና የዋንጫው አሸናፊ ለመሆን እጅግ የተቃረቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ ብቻ ድል አሳክተው በአንዱ ተሸንፈው በሁለቱ አቻ ቢወጡም ተከታያቸው ባህርዳር ከተማም በተመሳሳይ ነጥቦችን በመጣሉ የሠንጠረዡ አናት ላይ ተደላድለው እንዲቀመጡ አድርጓቸዋል። አምስት ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያስመረጡት ፈረሠኞቹ በቀጣይ ለሚያደርጓቸው ጨዋታዎች እነዚህን ተጫዋቾች በልምምድ ወቅት ለ 12 ቀናት ያህል አለማግኘታቸው ምናልባትም የሚመርጡት የጨዋታ መንገድ የተለየ ከሆነ ቶሎ ለማዋሃድ በመጠኑም ቢሆን ይቸገራሉ ካልተባለ ቡድኑ ያለበት የአሸናፊነት መንፈስ ዋንጫውን ለማንሳት የሚያግደው ነገር እንደሌለ ይጠቁማል።በአንጻሩ ደግሞ ተጫዋቾቹ የብሔራዊ ቡድኑ ጥሪ የሚፈጥርላቸው መነሳሳትም ይኖራል። የቡድኑም ሆነ የውድድር ዓመቱ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው እስማኤል ኦሮ አጎሮ የሊጉን የምን ጊዜውም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ለመጋራት ስድስት ጎሎች የሚቀሩት ሲሆን በቀጣይ በሚያደርጋቸው ሦስት ጨዋታዎች በአማካይ ሁለት ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ይኖርበታል። በዚህ ምክንያትም በነገው ጨዋታ ላይ ልዩነት ፈጣሪ ተጫዋች ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

በኢትዮጵያ ቡና በኩል መሐመድኑር ናስር እና አብዱልከሪም ወርቁ በጉዳት ጨዋታው የሚያልፋቸው ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ከተስፋ ቡድን ያደገው አማካይ አቤል በስተቀር አጠቃላይ የቡድኑ ተጫዋቾች ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው። ለወራት ከሜዳ የራቀው አማኑኤል ገብረሚካኤልም የተሟላ ልምምድ ማድረግ መጀመሩን ተከትሎ አስራ ስምንት ውስጥ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 45 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 21 ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 7 ጊዜ ድል ሲያደርጉ 17 ጨዋታዎች አቻ ተጠናቀዋል። 90 ግቦች በተቆጠሩበት የሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት ፈረሠኞቹ 61 ቡናማዎቹ ደግሞ 29 ግቦችን በስማቸው አስመዝግበዋል።

ባህር ዳር ከተማ ከሲዳማ ቡና

ምሽት 12 ሰዓት ላይ የጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር በ 54 ነጥቦች 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን የጣና ሞገዶቹ በ 35 ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡት ሲዳማ ቡናዎች ሲያገናኝ ለሻምፒዮንነት እና ላለመውረድ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ተከታታይ አምስት ድሎችን በብቸኝነት በማሳካት ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ ቡድን የነበሩት የጣና ሞገዶቹ ካለፉት ሰባት ጨዋታዎች ግን በሦስቱ ብቻ ድል በማሳካታቸው ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአምስት ነጥቦች ርቀው በመቀመጥ የዋንጫ ህልማቸው በሌላ ቡድን ውጤት ማጣት ላይ እንዲመሠረት አስገድዷቸዋል። ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዕኩል አምስት ተጫዋቾችን እና ዋና አሰልጣኛቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ላደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ማስመረጥ የቻሉት ባህር ዳሮች ለዋንጫው ያላቸው ተስፋ የመነመነ ቢመስልም ሁለተኛ ደረጃቸውን አረጋግጠው በቀጣይ ዓመት በአህጉር አቀፍ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የነገው ድል በቂያቸው ነው። ሆኖም ተጋጣሚያቸው ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ ፈታኝ ሆኖ እንደሚቀርብ ስለሚጠበቅ የሚገጥማቸው ፈተና ቀላል አይሆንም።
\"\"
ወድድሩ ወደ ሀዋሳ ከተማ ባመራ ማግሥት በበርካታ ደጋፊዎቻቸው ታጅበው አራት ተከታታይ የ 1-0 ድሎችን ማሳካት ችለው የነበሩት ሲዳማዎች የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎችን ግን በአቻ ውጤት አጠናቀዋል። እጅግ የተሻሻለው የተከላካይ መስመሩ በእነዚህ ስድስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስተናገዱ ከለገጣፎ ለገዳዲ በመቀጠል የሊጉ ሁለተኛው ከፍተኛ ግብ የተቆጠረበት የነበረው ቡድን ተሻሽሎ ላሳካቸው ድሎች ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስድ ነው። ሆኖም ከአምስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥብ ብቻ ወዳሳኩበት እና ማስታወስ የማይፈልጉትን ቆይታ ወዳደረጉበት የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በድጋሚ የሚመለሱት ሲዳማዎች የነገውን ጨዋታ ካሸነፉ ወደ 8ኛ ደረጃ ከፍ ብለው  አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንዲቀመጡ የሚያደርጋቸው ስለሆነ ጠንካራ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

የባህርዳር ከተማ ሙሉ የቡድኑ አባላት ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸው ሲገለጽ በተመሳሳይ ይገዙ ቦጋለ እና አንተነህ ተስፋዬ ከጉዳት የተመለሱለት ሲዳማ ቡናም ሙሉ ስብስቡን ይዞ ይቀርባል።

ተጋጣሚዎቹ እስካሁን ሰባት የሊግ ጨዋታዎችን እርስ በእርስ አድርገዋል። ባህር ዳር ከተማ ሦስት ሲዳማ ቡና ደግሞ ሁለት ጊዜ ማሸነፍ ሲችሉ ሁለት ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ባህር ዳር 10 ሲዳማ ቡና ደግሞ 9 ግቦች አስመዝግበዋል።