ሪፖርት | የሊጉ 46ኛ ሸገር ደርቢ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የተደረገው የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ለተመልካች ማራኪ ፉክክር ተደርጎበት 1-1 ተጠናቋል።

\"\"

ለኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ በተደረገው የሽኝት ፕሮግራም በጀመረው ጨዋታው የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ቢደረግባቸውም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ እና የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ብልጫውን የወሰዱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተለይም በሦስት አጋጣሚዎች የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር ችለው ነበር። 8ኛው ደቂቃ ላይ እስማኤል ኦሮ አጎሮ በግንባሩ በመግጨት ያሳለፈለትን ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘው አቤል ያለው ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። 15ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ናትናኤል ዘለቀ በግሩም ዕይታ ያቀበለውን ኳስ አግኝቶ ለግራ እግሩ ማመቻቸት የቻለው እስማኤል ኦሮ አጎሮ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ የግብ ዕድሉን ሲያባክነው በአንድ ደቂቃ ልዩነትም ሄኖክ አዱኛ ከረጅም ርቀት ያሻገረለትን ኳስ በሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘው ረመዳን የሱፍ ከማቀበል አማራጭ ጋር ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

ከራሳቸው የግብ ክልል ለመውጣት ተቸግረው የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በእንቅስቃሴ ደረጃ እየተነቃቁ በመምጣት 21ኛው ደቂቃ ላይ መስፍን ታፈሰ ከሳጥን ውጪ ባደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ የመጀመሪያ የግብ ሙከራቸውን ሲያደርጉ በአንድ ደቂቃ ልዩነትም ኃይለሚካኤል አደፍርስ በሳጥኑ የግራ ክፍል በድንቅ ሩጫ ይዞት ገብቶ ወደ ውስጥ ያሻገረውን ኳስ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው በመጠኑ እየተቀዛቀዙ የሄዱት ፈረሠኞቹ የአጋማሹን ብቸኛ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ 31ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ቢኒያም በላይ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው አቤል ያለው በግንባሩ በመግጨት ያደረገውን ሙከራ የቡናማዎቹ ግብ ጠባቂ በረከት አማረ በጥሩ ቅልጥፍና አስወጥቶታል። ቀሪዎቹ ደቂቃዎችም መጠነኛ ፉክክር ተደርጎባቸው አጋማሹ ያለ ግብ ተገባዷል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተሻሽሎ እና ይበልጥ ለተመልካች ማራኪ ሆኖ ሲቀጥል 55ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ያለው ከቀኝ መስመር ያሻገረውን እና ወልደአማኑኤል ጌቱ ያቋረጠውን ኳስ ያገኘው ናትናኤል ዘለቀ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም የተሳካ ቀን ያሳለፈው ግብ ጠባቂው በረከት አማረ በግሩም ብቃት መልሶበታል።

ጨዋታው 66ኛ ደቂቃ ሲደርስ በቅዱስ ጊዮርጊስ አማካኝነት ግብ ተቆጥሮበታል። ጋቶች ፓኖም ከሬድዋን ናስር በቀማው ኳስ ከቸርነት ጉግሣ ጋር ተቀባብሎ ይመታዋል ተብሎ ሲጠበቅ በድንቅ ዕይታ ለእስማኤል ኦሮ አጎሮ ሲያቀብል ኳሱን ለማስቆጠር በሳጥኑ የግራ ክፍል ምቹ ቦታ ላይ የነበረው አጎሮም መረቡ ላይ አሳርፎት ቡድኑን መሪ ሲያደርግ የራሱን የግብ መጠንም 24 ማድረስ ችሏል።

ጥሩ የኳስ ቁጥጥር ይኑራቸው እንጂ የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር የተቸገሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች 72ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ባደረጉት የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ግብ አስቆጥረዋል። አማኑኤል ዮሐንስ ከሮቤል ተክለሚካኤል በተቀበለው ኳስ ከፍ አድርጎ ለብሩክ በየነ በግሩም ዕይታ ሲያቀብል ብሩክ በየነም ኳሱ ዐየር ላይ እንዳለ እጅግ አስደናቂ በሆነ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎት ቡድኑን አቻ አድርጓል።

76ኛው ደቂቃ ላይ ለረጅም ወራት ከሜዳ ርቆ የቆየው የፈረሰኞቹ የመስመር አጥቂ አማኑኤል ገብረሚካኤል ተቀይሮ በመግባት ወደ ሜዳ ሲመለስ 85ኛው ደቂቃ ላይ የቡናማዎቹ አማካይ አማኑኤል ዮሐንስ ተጫዋች በማለፍ ከሳጥን ውጪ ጥሩ ሙከራ አድርጎ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ሲቀር በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ደግሞ እስማኤል ኦሮ አጎሮ በግንባሩ በመግጨት ሁለት ሙከራዎች አድርጎ ዒላማቸውን ሳይጠብቁ ወጥተውበታል። በአንጻሩ ተቀይሮ የገባው የቡናው ታዳጊ አማኑኤል አድማሱም ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር። ጨዋታውም 1-1 ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ከታክቲክ በላይ ጨዋታው ደርቢ መሆኑ ከባድ እንዲሆን እንዳደረገው ነገር ግን ጨዋታው በጣም ጥሩ እንደነበር ሲገልጹ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የነበራቸው አለመረጋጋት እና የውሳኔ ችግር ግብ ላለማስቆጠራቸው እንደ ምክንያት በመጥቀሰ ግብ ያስተናገዱትም በራሳቸው ስህተት እንደሆነ ተናግረዋል።

\"\"

የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ በበኩላቸው ጨዋታው ጥሩ እንደነበር እና የሁለቱም ቡድኖች አቀራረብ ጠንካራ እንደነበር ሲናገሩ ሮቤል ተክለሚካኤልን ባልተለመደ ቦታ ያሰለፉት በቦታው የሰው ዕጥረት በመኖሩ እና ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ባደረጉት ጨዋታ ጥሩ ስለነበር እንደሆነም ገልጸዋል። አሰልጣኙ አክለውም በመጀመሪያው አጋማሽ መሃል ሜዳው ላይ ብልጫ ለመውሰድ አልመው በመግባታቸው ወደፊት ብዙም እንዳልሄዱ ከዕረፍት መልስ ግን በመነጋገር ወደፊት ሄደው በመጫወት ግብ እንዳገኙ እና ግብ አስቆጣሪው ብሩክ በየነንም እስካሁን የጠበቁት አቅም ስላለው እንደሆነ ሲናገሩ እንዲህ ዓይነት ትልቅ ጨዋታ ላይ ግብ ማስቆጠሩ ደግሞ ከዚህ በኋላ ያለው ጨዋታ እንዲቀለው እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።