መቐለ 70 እንደርታ ወደ ልምምድ ተመልሷል

የ2011 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮኖቹ መቐለ 70 እንደርታዎች ልምምድ ጀምረዋል።

\"\"

ምዓም አናብስት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የነበራቸው ተሳትፎ ጦርነቱን ተከትሎ ከተቋረጠ በኋላ ዳግም ወደ እንቅስቃሴ ለመመለስ በመጣር ላይ ይገኛሉ። በዚህ መሰረት በአሰልጣኝ ጎይትኦም ኃይለ ፣ ቴክኒክ ዳይሬክተር ገብረኪሮስ አማረ ፣ ክለቡን ለረዥም ጊዜ በቡድን መሪነት ያገለገለገው ተኽለ እያሱ እና ጌታቸው ዘርዑ እየተመሩ ወደ እንቅስቃሴ ገብተዋል። ለጊዜው ዘጠኝ ተጫዋቾች ይዞ በቀን አንዴ ልምምድ በመስራት ላይ የሚገኘው ክለቡ በቀጣይ ከጦርነቱ በፊት የክለቡ አባላት የነበሩ ተጫዋቾች ወደ ስብስቡ እንደሚቀላቅል ለማወቅ ተችሏል።

\"\"

ክለቡ ምንም እንኳን በተለያዩ አካላት ድጋፍ፤ በተወሰኑ የልብ ደጋፊዎች እገዛ እና የአሰልጣኞች የግል ጥረት የተወሰኑ ድጋፎች ቢያገኝም በተሻለ መንገድ ወደ እንቅስቃሴ ለመግባት አሁንም ድጋፎች እንደሚያስፈልጉት የክለቡ አሰልጣኞች ነግረውናል። ከሳምንታት በፊት የክለቡ አመራሮች እና የመቐለ ከተማ መስተዳድር ተወካይ በጋራ ሆነው በክለቡ ቀጣይ እርምጃዎች ዙርያ መግለጫ በተሰጠበት መድረክ የከተማው መስተዳደር ክለቡን ለመመለስ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ቃል መግባቱ ይታወሳል። ሆኖም የክለቡን ልምምድ ለመመልከት ወደ ስፍራው ባቀናንበት ሰዓት ለቡድኑ በቂ የሆነ ትኩረት እንዳልተሰጠ ለመመልከት ችለናል።