ሪፖርት | ዐፄዎቹ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሰዋል

በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ፋሲል ከነማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2-1 በመርታት ነጥቡን ከአርባ አሻግሯል።

\"\"

ምሽት 12:00 ላይ በጀመረው ጨዋታ ቀዳሚ ደቂቃዎች ፈጠን ያሉ ጥቃቶች ወደ ሁለቱም ግቦች ሲሰነዘሩ ተስተውሏል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ኳስ በማንሸራሸር እና ለግብ በመቅረብ ፋሲል ከነማ ደግሞ ከቆሙ ኳሶች እና ከሳጥን ውጪ በሚደረጉ ሙከራዎች ተጋጣሚያቸውን ለመፈተን ሞክረዋል። በተለይም 13ኛው ደቂቃ ላይ ይሁን እንዳሻው ከኦሴይ ማዉሊ በመቀበል ከግራ የሳጥኑ መግቢያ ላይ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት የወጣበት ቅፅበት ፋሲልን መሪ ለማድረግ የቀረበ ነበር።

በመሀል ሜዳ ፉክክር ተገድቦ በቀጠለው ጨዋታ ኤሌክትሪኮች የተሻለ ኳስ ቢይዙም 29ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ በኩል የቡድኑ የጥቃት መነሻ ሆኖ ይታይ የነበረው ዮናስ ሰለሞን ከግራ የደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ካደረግው ሙከራ በፊት ሚኬል ሳማኬን መፈተን አልቻሉም ነበር። በሌላ በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ በዋለው ኦሳይ ማዉሊ የሳጥን ውጪ ሙከራዎች ምላሽ መስጠት የቀጡሉት ፋሲሎች 40ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚ ሆነዋል። ፋሲሎች ከሜዳቸው በንክኪዎች ያወጡትን ኳስ ኦሴይ ማዉሊ ከመሀል ሜዳ ግሩም ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ አድርሶት ዓለምብርሀን በግራ ሳጥኑ መግቢያ ላይ ደርሶ ግብ አድርጎታል።

ከዕረፍት መልስ ኤሌክትሪኮች ስንታየሁ ዋለጬ ከቀኝ አቅጣጫ ሞክሮት የጎን መረብ ላይ ባረፈው ሙከራ የተነቃቁ ቢመስሉም ብዙም ሳይቆይ 50ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ጎል አስተናግደዋል። ዱላ ሙላቱ በረጅም የደረሰውን ኳስ አብርዶ ከቀኝ ወደ ውስጥ ሲያመቻችለት ኦሴይ ማዉሊ ከሳጥን ውስጥ ዞሮ በመምታት የካክፖ ሸሪፍዲን መረብ ላይ አሳርፏል። ጋናዊው አጥቂ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም ያለቀለት ዕድል አግኝቶ ሌላ ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር። በቀጣዮቹ ደቂቃዎችም የኤሌክትሪኮች የርቀት ሙከራ አልፎ አልፎ ይታይ እንጂ ፋሲሎች በቀኝ መስመር በዱላ ሙላቱ አቅጣጫ የሚሰነዝሯቸው ጥቃቶች ጎልተው መታየታቸውን ቀጥለዋል።

በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች የዐፄዎቹ የእንቅስቃሴ የበላይነት ከፍ ብሎ ቢታይም በተጋጣሚ ሳጥን መግቢያ ላይ በደካማ የቅብብል ውሳኔዎች ምክንያት ከርቀት ሙከራዎች ውጪ ካለቀላቸው የግብ ዕድሎች ርቀው ታይተዋል። ይልቁኑም 87ኛው ደቂቃ ላይ አብዱርሀማን ሙባረክ የፀጋ ደርቤን የማዕዘን ምት በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ልዩነቱን ማጥበብ ችሏል። በቀሪ ደቂቃዎችም ኤሌክትሪኮች የአቻነት ግብ ፍለጋ ተጨማሪ ጥረቶችን ቢያደርጉም ጨዋታው በፋሲል ከነማ 2-1 አሸናፊነት መጠናቀቁ አልቀረም። በዚህም አፄዎቹ ነጥባቸውን 42 አድርሰው ለ4ኛነት መፎካከራቸውን ቀጥለዋል።

\"\"

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ቅጣው ሙሉ ተጫዋቾቻቸው ከዕረፍት በፊት ጥሩ መንቀሳቀሳቸውን እንዲሁም አዳዲስ ተጫዋቾችን መሞከራቸውን አንስተው ኳሶች መሳታቸው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ተፅዕኖ እንደነበረው አንስተዋል። አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በበኩላቸው በበርካታ ምክንያቶች የሜዳሊያ ደረጃ ባይሳካላቸውም የተሻለ ደረጃ ይዘው ለማጠናቀቅ እንደሚሞክሩ ተናግረው የወጣት ተጫዋቾቻቸውን እና የኦሴይ ማዉሊን የዕለቱ እንቅስቃሴ አድንቀዋል።