የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአሜሪካ ጉዞን በተመለከተ መግለጫ ተሰጠ

በመጪው ሐምሌ ወር መጨረሻ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለወዳጅነት ጨዋታዎች ወደ አሜሪካ የሚያደርገውን ጉዞ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን እና ጨዋታውን ያዘጋጀው ሲጂኤ ኒውማን በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

ዛሬ ከቀትር በኋላ በፌደሬሽኑ ፅ/ቤት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጨዉ ሐምሌ 26 ከጉያና ብሔራዊ ቡድን በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ እንዲሁም ሀምሌ 29 ላይ ደግሞ በአትላንታ ከተማ ከአትላንታ ዮናይትድ ጋር የሚያደርጋቸውን ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን በተመለከተ በተሰጠው በዚሁ መግለጫ ላይ ፌደሬሽኑን በተመወከል ዋና ፀሀፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን የተገኙ ሲሆን ጨዋታውን ባዘጋጀው እና በፊፋ እውቅና ያለው የጨዋታ አገናኝ የሆነውን ሲጂኤ ኒውማን በመወከል አቶ ዳዊት አርጋው ለመገናኛ ብዙሃን አባላት ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

\"\"

መግለጫውን በንግግር የከፈቱት አቶ ባህሩ ጥላሁን ተቋማቸው መቀመጫውን በሀገረ አሜሪካ ካደረገው ሲጄኤ ኒው ማን ከተሰኘው ተቋም ጋር በጋራ በመሆን ብሔራዊ ቡድን ወደ አሜሪካ ተጉዞ ጨዋታዎችን እንዲያደርግ ጥረት ሲያደርግ እንደነበር አንስተው ፤ ይህን ጉዞ ለማድረግ ከዚህ ቀደም በሁለት አጋጣሚዎች ታስቦ የነበረ ቢሆንም ብሔራዊ ቡድናችን የቻን አፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ በመሆኑ እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች ሳይሳካ መቅረቱን ተከትሎ ጉዞው ሐምሌ ወር መሸጋሸጉን ገልፀዋል።

የፌደሬሽኑ ዋና ፀሀፊ አያይዘውም አስቀድሞ ይፋ በተደረገው መሠረት በሐምሌ 1 እና ሐምሌ 8 ጨዋታዎችን ለማድረግ ቢታሰብም ወደ አሜሪካ ለመግባት ቪዛ የማግኘት ሂደቱ ውስብስ እንደመሆኑ እና በተጠቀሰው በሀገረ አሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የስፖርት ፌስቲቫል የሚደረግበት ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ውድድሩን በዚህ ወቅት ማካሄዱ ከጉዞው ተቀዳሚ አላማዎች ማለትም በሃገረ አሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር ብሔራዊ ቡድን ትስስር እንዲፈጠር ማድረግ ሆነ ብሔራዊ ቡድን በፋይናንስ ተጠቃሚ እንዲሆን በር መክፈት ከመሆኑ አንፃር ቀኑ ከዚህ አግባብ ወደ ሐምሌ መጨረሻ መገፋቱን አንስተዋል ፤ በገለፃቸውም የጉዞው የመጓጓዣ ሆነ በቆይታ ወቅት የሚኖሩ ሌሎች የቡድኑ ወጪዎች በሙሉ በሲጂኤ ኒው ማን የሚሸፈኑ ናቸው ሲሉም ገልፀዋል።

በማስከተል ደግሞ ገለፃ ያደረጉት የሲጂኤ ኒው ማን ተወካይ የሆኑት አቶ ዳዊት አርጋው ይህ ጉዞ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፈር ቀዳጅ መሆኑን አንስተው ይህን ጅምር ከወዳጅነት ጨዋታ ባለፈ በአሜሪካ ተቀማጭነታቸውን ካደረጉ ተቋማት ጋር በስፖንሰርሺፕ ሆነ በመሰረተ ልማት ግንባታ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፈርጀ ብዙ ጥቅም ይኖረዋል ሲሉ አውስተዋል።

\"\"

በማስከተል በስፍራ ከተገኙ የመገናኛ ብዙሃን አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሾች የተሰጡ ሲሆን ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል የጉያና ብሔራዊ ቡድን ስለተመረጠበት አግባብ ለቀረበው ጥያቄ አቶ ዳዊት ተከታዩን ብለዋል።

\”በቅድሚያ ተስማምተን የነበረው ከትሪንዳድ እና ቶቢጎ እንዲሁም ከጃማይካ ብሔራዊ ቡድን ጋር ነበር ፤ ነገር ግን በቅርቡ በተካሄደው የኮንካካፍ አህጉራዊ ውድድር ላይ ሁለቱም ብሔራዊ ቡድኖች ከታፋይ መሆናቸውን ተከትሎ ሳይካ ቀርቷል። ነገር ግን የጉያና ብሔራዊ ቡድን ምንም እንኳን ሦስተኛ ምርጫችን የነበረ ቢሆንም ብሔራዊ ፌደሬሽናቸው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ካለው ትልቅ አክብሮት እና ከአፍሪካ ብሔራዊ ቡድን ጋር ጨዋታ አድርገው ባለማወቃቸው የተነሳ በእነሱ በኩል በነበረ ከፍተኛ ፍላጎት መነሻነት እና እኛም ለጉዞው የመረጥነው ወቅት ከጎልድ ካፕ ጋር በመቀራረቡ መነሻነት ይህን አማራጭ ወስደናል።\”

አቶ ባህሩ በበኩላቸው ደግሞ ወደስፍራው ስለሚያቀናው ልዑክ ለቀረበላቸው ጥያቄ ይህን ብለዋል።

\”በዚህ ጉዞ ውስጥ ተጫዋቾች እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ባለፈ በጉዟቸው የተለያዩ ጉዳዮች ታሳቢ አድርገን እንደመጓዛችን ይህን ለማድረግ የሚረዱ አመራሮችም ይካተታሉ። በቁጥር መጥቀስ ካስፈለገም ከ32 ያልበለጠ ሰው ይዘን ወደ ስፍራው እናቀናለን። ከዚህ ቀደም ወደ ሌሎች ሀገራት እንደምናደርጋቸው ጉዞዎች በርከት ያለ ሰው ይዘን ላንሄድ እንችላለን።\”

በቀጣይም ፌደሬሽኑ ከትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች ጋር በተያያዘ በስፔን ሀገር መቀመጫውን ካደረ አንድ ተቋም እና ፊፋ ጋር በትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች ዙርያ መጠነ ሰፊ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝና በቅርቡም የምስራች ሊኖር እንደሚችል የተገለፀበት መግለጫ ፍፃሜውን አግኝቷል።