መረጃዎች| 110ኛ የጨዋታ ቀን

በነገው ዕለት በሚካሄዱ ሁለት የ29ኛ ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ዙሪያ ተከታዮቹን መረጃዎች አቅርበናል።

ለገጣፎ ለገዳዲ ከ ሲዳማ ቡና

መውረዱን ያረጋገጠው ለገጣፎ ለገዳዲ እና በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኘው ሲዳማ ቡና የሚያደርጉት ጨዋታ ነገ 09:00 ላይ ይጀምራል።

ለገጣፎዎች መውረዳቸው ካረጋገጡ በኋላ ሳይጠበቅ መሻሻሎች አሳይተዋል። ቀድሞ ደካማ አጥቂ ክፍል የነበራቸው አሰልጣኝ ዘማርያም በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ግብ ያላስቆጠሩበት ጨዋታ አልነበረም። አዳማ ከተማን አሸንፈው ከኢትዮጵያ ቡና ጋርም አቻ መለያየታቸውም ይታወሳል። ይህንን ተከትሎም በነገው ጨዋታ ቢያንስ ቢያንስ ቀላል ተጋጣሚ እንደማይሆኑ መገመት ይቻላል። በመጀመርያው ዙር በሲዳማ የሁለት ለባዶ ሽንፈት የገጠማቸው ለገጣፎዎች ምንም እንኳን ቀድመው መውረዳቸውን በማረጋገጣቸው በነጥብ ረገድ የነገው ጨዋታ ፋይዳ ቢስ ቢሆንም ከጫና ውጭ ሆነው መጫወታቸው የሚሰጣቸውን የሥነ-ልቦና ብልጫ ሲታይ ግን ቀላል ግምት እንዳይሰጣቸው ያደርጋል።

\"\"

በአዳማ ከተማ የሦስት ለአንድ ሽንፈት ከገጠማቸው በኋላ በተደረጉ ሰባት ጨዋታዎች ሽንፈት ያልቀመሱት ሲዳማዎች በጥሩ ወቅታዊ አቋም ከሚገኙ ቡድኖች ውስጥ ይጠቀሳሉ። በአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ስር የሚያስደንቅ ለውጥ አድርገው በጥሩ የድል ጎዳና ይገኛሉ። በመጨረሻው ጨዋታ ጠንካራውን ባህር ዳር ከተማን ረምርመው ወደዚህ ጨዋታ መግባታቸውም ትልቅ የሞራል ስንቅ እንደሚሆናቸው ግልፅ ነው። በተጠቀሱት ሰባት ጨዋታዎችም ዘጠኝ ግቦች አስቆጥረዋል ፤ ይህ ማለት በአማካይ 1.2 ጎሎች ማለት ነው። ሌላው የቡድኑ ጥንካሬ የተከላካይ ክፍሉ ነው። ቡድኑ ከፍተኛ መሻሻል ባሳየባቸው ከሰባቱ ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ግብ ተቆጥሮበታል። ግቧ ከአርባ ምንጭ ጋር አቻ በተለያየበት ጨዋታ አሕመድ ሁሴን ያስቆጠራት አንድ ግብ ነበርች። የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እና ቁጥሮች እንደሚያሳዩት ሲዳማ ቡና በጥሩ ወቅታዊ አቋም ይገኛል። ከወራጅ ቀጠና ተነስቶ በሠላሳ ስምንት ነጥቦች በስምንተኛ ደረጃ መቀመጡም ሌላው የቡድኑ መሻሻል ትልቅ ምስክር ነው።

በጨዋታው ለገጣፎዎች በቅጣትም ሆነ በጉዳትም የሚያጡት ተጫዋች የሌለ ሲሆን ሲዳማዎች ግን ጊት ጋትኩትን በቅጣት ምክንያት አያሰልፉም።

ኢትዮጵያ ቡና ከ መቻል

ሁለቱን የመዲናዋ ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ ነገ ምሽት 12:00 ላይ ይከናወናል።

በሸገር ደርቢ አቻ ተለያይተው ወደ ነገው ጨዋታ የሚቀርቡት ቡናማዎቹ በሰላሳ ዘጠኝ ነጥቦች በስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ወጥ የሆነ አቋም ማሳየት የተሳናነው በአሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ የሚመራው ስብስብ ከፍተኛ የሆነ ግብ የማስቆጠር ችግር ይታይበታል።

ለመጨረሻ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎችም ሀድያ ሆሳዕናን ባሸነፈበት አንድ ጨዋታ ብቻ ነው ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር የቻለው። ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት አስር ጨዋታዎች በሁለቱ ብቻ መረቡን ሳያስደፍር የወጣው እና አስራ ሁለት ግቦች ያስተናገደው የቡድኑ ተከላካይ ክፍል የነገው ተጋጣሚው መቻል የአጥቂ ክፍል በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኝ እንደ መሆኑ መሻሻሎች ያስፈልገዋል። በቡድኖች መሀል ያለው የነጥብ ቅርርብ ጥቂት መሆን እና ቡድኑ ደረጃውን አሻሽሎ ዓመቱን ለመጨረስ ያለው ዕድል ከፍተኛ በመሆኑ በነገው ጨዋታ ጠንክሮ እንዲቀርብ ያስገድዱታል።

በመጨረሻው ሳምንት ወልቂጤን አሸንፈው መጠነኛ እፎይታ ያገኙት መቻሎች በሰላሳ ሰባት ነጥብ በአስረኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

\"\"

መቻሎች በጊዜ ሂደት ግብ የማስቆጠር ችግራቸው ፈተው በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ቢያስቆጥሩም የተከላካይ ክፍላቸው ላይ ግን መሻሻሎች አልታዩም። በተጠቀሱት አምስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች አስተናግደዋል። በነገው ጨዋታ ምንም እንኳን ግብ የማስቆጠር ችግር ያለበት ቡድን ቢገጥሙም የኢትዮጵያ ቡና አጥቂዎች ፈጣን መሆን ነገሮች አይቀያይርም ብሎ መገመት አይቻልም። በነገው ጨዋታም በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኘውን የአጥቂ ክፍላቸው ጠንካራ ጎኖች ማስቀጠል ከጨዋታው ነጥብ ይዘው እንዲወጡ እንደሚረዳቸው ይታመናል።

በነገው ፍልሚያ ኢትዮጵያ ቡናዎች ሬድዋን ናስር ፣ አብዱልከሪም ወርቁ ፣ መስፍን ታፈሰ ፣ መሐመድኑር ናስር ፣ ኩዋኩ ዱሀ እና እዝቄል ሞራኬን በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም። በመቻል በኩል ደግሞ በኃይሉ ግርማ እና ተስፋዬ አለባቸው በቅጣት
ፍፁም ዓለሙ እና ኢብራሂም ሁሴን በጉዳት ጨዋታው ሲያልፋቸው የምንይሉ ወንድሙ እና ተሾመ በላቸው መሰለፍም አጠራጣሪ ሆኗል።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ 31 ጨዋታዎችን አድርገዋል። ኢትዮጵያ ቡና 15 ጊዜ በማሸነፍ የበላይ ሲሆን መቻል 7 ጊዜ ድል አድርጎ በ9 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ቡና 45 መቻል ደግሞ 32 ግቦችን አስቆጥረዋል።