የባህል እና ስፖርት ሚኒስተር እንዲሁም የእግርኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች በመቐለ ጉብኝት አድርገዋል

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳያስ ጂራ እና የትግራይ ክልል እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ነጋ አሰፋ በወቅታዊ ሁኔታዎች ዙርያ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ባህል እና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ ፣ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚደንት አቶ ኢሳያስ ጅራ የተመራ የልዑካን ቡድን በመቐለ ከተማ ተገኝተው የክልሉን አሁናዊ እግርኳሳዊ ሁኔታ ተመልክተዋል። ጠዋት በነበረው መርሐግብር ትግራይ ስታዲየምን ጨምሮ የተለያዩ የስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎችን ተዘዋወረው ሲመለከቱ ከምሳ ሰዓት በኋላ ደግሞ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

አቶ ኢሳያስ ጅራ በሰጡት ሀሳብ የጀመረው ይህ መግለጫ በርካታ ጉዳዮች ተነስተውበታል። መጀመርያ ላይ ሀሳባቸው የሰጡት አቶ ኢሳያስ ጅራ ወደ ትግራይ መጥተው ሁኔታውን ለማየት እንደዘገዩ ገልፀው ለዚህ ምክንያትም ሁኔታዎች አለመመቻቸት እንደሆነ ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ ቀጥለውም ትግራይ ክልልን እግርኳስ ለማገዝ ቁርጠኛ እንደሆኑ ገልፀው ፤ የትግራይ ስቴድየም ሁኔታ ከተመለከቱ በኋላ እንደ መንግሥት ስታዲየሙን ለመጠገን ኃላፊነት እንደተወሰደም ጠቅሰዋል \” እንደፌደሬሽን ሳይሆን እንደ መንግሥት የደረሰውን ውድመት ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ሥራውን ለመጨረስ ብዙ ወጪ ይጠይቃል። ነገር ግን መስራት በምንችለው ሁኔታ ሳሩን እና መልበሻ ክፍሉን መስራት ከተቻለ የከተማው ህዝብ መታደግ ነው። ውድድሮች ወደዚህ መምጣት ከቻሉ የመዝናኛ አማራጭ ከማስፋትም በላይ ጥቅም አለው። ይህንን ኃላፊነትም ሚኒስተር መስርያ ቤቱ እና ግዚያዊ መስተዳድሩ ወስደዋል\” ብለዋል።

\"\"

ፕሬዝዳንቱ ቀጥለውም \”ጦርነቱ ከተነሳ በኋላ ፌደሬሽናችን የአንድ ዓመት ጊዜ ሰጥቶ ነበር። ከዛ ውጭ ከሆነ ግን ወደ ክልል ውድድር ይመለሳል ነው የሚለው ህጋችን። ግን ይሄን ነገር እንዴት ማየት እንችላለን በሚል ጉዳይ ከስራ አስፈፃሚው ጋር እየተነጋገርን ነው። በጣም ወጣ ያለ ነገር አትጠብቁ ህጎች አሉን ፤ ህጉን መሰረት አድርገን እና የነበረው ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ አስገብተን የምንወስን ይሆናል። እዚህ መድረክ ልላይ ሆኜ እንዲህ እንዳደርጋለን ብዬ መዋሸት አልችልም\” ብለዋል።

አቶ ኢሳያስ ጨምረውም ዋና ዓላማቸው መሰረቱን ማስተካከል ነው ካሉ በኋላ \”አቅማችን የፈቀደውን እናደርጋለን፤ ለዛሬ ግን አንድ ሚልየን ብር ለፌደሬሽኑ ድጋፍ አድርገናል። በቀጣይም ግንኙነታችን እናጠናክራለን የማቴርያል ድጋፎችም እናደርጋለን።\” ብለዋል።

ቀጥለው ሀሳባቸውን የሰጡት የክልሉ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ነጋ አሰፋ በትግራይ ክልል በኩል ክለቦች ወደ ነበሩበት ሊግ እንዲመለሱ ፅኑ ፍላጎት እንዳለ ገልፀዋል፤ \” በትግራይ ክልል በኩል ክለቦቹን የመመለስ ጥያቄ ከባድ ነው። ይህ ማሕበረሰባዊ ፣ ፖለቲካዊ እና የኢኮኖሚ ጥያቄ ነው\” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ቀጥሎም ክለቦቹ ማሕበረሰባዊ ትስስር በመፍጠር ፣ ለዲሞክራስያዊ ስርዓት ግንባታ ትልቅ አስተዋፅኦ በማድረግ እና ኢኮኖሚው በማነቃቃት ረገድ ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳደረጉ ገልፀዋል።

\"\"

በመድረኩ የተገኙት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሸረፋ ደሎቾ በበኩላቸውም \”ሥልጠና ያመለጣቸው ዳኞች መቐለ ድረስ ባለሞያዎች ልከን ስልጠና እንሰጣቸዋለን\” ብለዋል።

መጨረሻ ላይ ስለክለቦቹ ወደ ሊግ የመመለስ ጉዳይ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ኢሳያስ ጅራም ውሳኔ ለመስጠት እንደማይቻኮሉ ገልፀዋል \” ግልፅ የሆኑ ነገሮች አሉ እነሱን ወስነን ማስቀመጥ እንችል ነበር። ግን የነበሩ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ አስገብተን በአመራር ደረጃ አይተን የምንወስነው ነገር ነው። ይህ ማለት ግን እስካሁን ድረስ ምንም ሳይታይ ተንከባሎ እዚህ የደረሰ ጉዳይ አይደለም፤ የሥራ አስፈፃሚ ስብሰባ ሚስጢራዊ ነው ይህን ተነጋግረናል ይሄን ወስነናል አልላችሁም ፤ ቀጣይ የሚታይ ነገር ነው\” ብለዋል።