ሪፖርት | የዐፄዎቹ እና ቡናማዎቹ ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል

የውድድር ዓመቱ የመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት የመጀመሪያ መርሐግብር የነበረው የፋሲል ከነማ እና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ 0-0 ተገባዷል።

በውድድር ዓመቱ የመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት የመጀመሪያ መርሐግብር ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡናን ሲያገናኝ 9 ሰዓት ላይ ጅማሮውን ባደረገው ጨዋታ መጠነኛ ፉክክሮች በተደረጉባቸው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ዐፄዎቹ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ቡናማዎቹ ደግሞ ዝግ ባለ እና በበርካታ ቅብብሎች የታጀበ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲሞክሩ ተስተውሏል።

በጨዋታው ሩብ ደቂቃዎች ከተቆጠሩ በኋላ የጨዋታውን ሚዛን ወደ ፋሲል ከነማ እየተደፋ ሄዷል። ሆኖም በጥቂት ቅብብሎች ወደ ሳጥን  መድረስ የቻለው ቡድኑ የአጋማሹን የተሻለ ሙከራ 27ኛው ደቂቃ ላይ አድርጓል። መናፍ ዐወል ከረጅም ርቀት ያሻገረለትን ኳስ በጥሩ ቅልጥፍና ተቆጣጥሮ በሳጥኑ የግራ ክፍል በኩል መግባት የቻለው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው ሱራፌል ዳኛቸው ያደረገው ሙከራ በግቡ የላይ አግዳሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ወጥቶ የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ከዕረፍት መልስ ተሻሽለው የቀረቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን በማጠናከር የጠሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲችሉ 49ኛው ደቂቃ ላይም በጨዋታው የመጀመሪያውን ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም አብዱልሃፊዝ ቶፊቅ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ማኑኤል አድማሱ በደካማ አጨራረስ ሳይጠቀምበት ሲቀር 58ኛው ደቂቃ ላይም ብሩክ በየነ ከቅጣት ምት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሚካኤል ሳማኪ መልሶበታል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተቀዛቅዘው የቀረቡት ፋሲሎች 64ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው ከሳጥን ውጪ ካደረገው ሙከራ ውጪ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ 73ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ብቸኛውን ዒላማ የጠበቀ ሙከራቸውን አድርገዋል። ኦሴይ ማውሊ ሱራፌል ዳኛቸው ከእጅ ውርወራ ባቀበለው ኳስ ተከላካዮችን በግሩም ክህሎት አታልሎ ኳሱን በማመቻቸት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ መልሶበታል። ሆኖም በሴኮንዶች ልዩነት ኢትዮጵያ ቡናዎች በጥሩ የመልሶ ማጥቃት ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር። አማኑኤል አድማሱ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ብሩክ በየነ ኳሱን ሳይቆጣጠረው ቀርቶ የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

\"\"

በመጨረሻ 20 ደቂቃዎች በመጠኑ በመነቃቃት በተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ዐፄዎቹ 81ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ዱላ ሙላቱ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ በግሩም ሁኔታ በአንድ ንክኪ የተቆጣጠረው ኦሴይ ማውሊ ኳሱ በዓየር ላይ እንዳለ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። ጨዋታውም ያለ ግብ ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች  የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የፋሲል ከነማን አመራሮች እና ደጋፊዎች አሰልጣኝ ላይ ጫና የማይፈጥሩ በመሆናቸው ምስጋና ካቀረቡ በኋላ ቡድኑ ላይ የሠሩት ነገር የተሻለው ነገር  ናትናኤል ገብረጊዮርጊስን በተለያየ ቦታ እንዲጫወት ማስቻላቸው መሆኑን በመናገር ለሚመጣው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ መልካም ምኞት በመግለጽ በየክለቦች የሚታየው የተጫዋቾች የዲስፕሊን ጉድለት እንደ ሀገር መስተካከል እንዳለበት አሳስበዋል። የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ በበኩላቸው ቡድኑ እንደ አዲስ በመዋቀሩ ጊዜ እንደሚያስፈልገው በመናገር በቀጣይ ጊዜያት ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል በመጠቆም ሀሳብ የሚቀበሉ አሰልጣኝ እንደሆኑ ገልጸዋል።

\"\"