አማኑኤል ገብረሚካኤል ነገ ወደ ደቡብ አፍሪካ ያመራል

ኢትዮጵያዊው አጥቂ በደቡብ አፍሪካው ክለብ ሞሮካ ስዋሎስ የሙከራ ጊዜ ለማሳለፍ ነገ ዕሁድ ረፋድ ወደ ስፍራው ይጓዛል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ያለፉትን ተከታታይ ዓመታት በወጥ አቋማቸው ስማቸውን ከፍ ካደረጉ ተጫዋቾች መካከል አማኑኤል ገብረሚካኤል አንዱ ነው።

\"\"

ከደብረብርሀን ከተማ እግርኳስን ከጀመረ በኋላ በመቐለ 70 እንደርታ በፕሪምየር ሊጉ እየደመቀ በበርካቶች ዐይን ውስጥ የሰረፀው ተጫዋቹ በመቀጠል ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ አምርቶ ያለፉትን ሦስት ዓመት ከግማሽ በክለቡ እየተጫወተ ቆይታን አድርጓል። ከመቐለ ጋር የሊግ ዋንጫን ያነሳው እና በፈረሰኞቹ ቤት በተከታታይ የሊግ ክብርን ያሳካው ተጫዋቹ ከተመሠረተ 76 ዓመታትን የደፈነው የደቡብ አፍሪካውን ሞሮካ ስዋሎስን ለመቀላቀል ጥቂት የሙከራ ቀናትን ለማሳለፍ ነገ ዕሁድ ረፋድ ወደ ስፍራው እንደሚያመራ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቋል።

\”ዛሬ ጨዋታዬን እንደጨረስኩ ዕሁድ ጠዋት እሄዳለሁ ፣ ያለውን ነገር የምወስነው እዛው ነው ፣ እንዴት እንደሆነ አላወኩም ለሙከራ ብዬ ቪዛም ስለተቀበልኩ ፣ አብዛኛው ፐርሰንት ለመፈረም ነው የምሄደው እነርሱ የሚሉት ግን ሙከራም አለው ነው። እኔ በጉዳትም ትንሽ ስለቆየው ቼክ ሊያደርጉኝ ይፈልጋሉ።\” ሲል ሀሳቡን አጠር አድርጎ ነግሮናል።

\"\"

ማሜሎ ዲ ሰንዳውንስ ሻምፒዮን በሆነበት የተጠናቀቀው የደቡብ አፍሪካ ዲኤስቲቪ ፕሪምየር ሊግ ውድድር በሀገሪቱ ዜግነት ባላቸው አሰልጣኝ ሙሳ ኒያታማ የሚመራው ሞሮካ ስዋሎስ ሊጉን በ40 ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ አጠናቋል።