​29 ወይስ 31 ?

ቅዱስ ጊዮርጊስ ባሳለፍነው ሳምንት ዕሁድ የዘንድሮው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን ሲያረጋግጥ ባጋራናቸው መረጃዎች ላይ ክለቡ በታሪኩ ለ29ኛ ጊዜ የሊግ ቻምፒዮን መሆኑን ገልፀናል። በትናንትናው ዕለትም ቅዱስ ጊዮርጊስ የዋንጫ ሥነስርዓቱን ሲያከናውን በተመሳሳይ ሁኔታ 29ኛ ድሉን ስለማሳካቱ ስንጠቅስ ቆይተናል። ይህንንም ተከትሎ ከበርካታ ተከታታዮቻችን የቅዱስ ጊዮርጊስ የቻምፒዮንነት ቁጥር 31 በመሆኑ እርምት እንድናደርግ መልዕክቶች አድርሰውናል። እኛም ገፍቶ የመጣውን ጥያቄ በመንተራስ 29ኛ ያልንበት ምክንያት እንደሚከተለው እናስቀምጣለን።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ፕሪምየር ሊጉ በ1990 በአዲስ ቅርፅ ከጀመረ ወዲህ ለ16ኛ ጊዜ ቻምፒዮን መሆኑ ዕሙን ነው። ሆኖም ከዛ ቀደም በነበረው የውድድር ቅርፅ ፈረሰኞቹ 1942 ላይ የመጀመሪያ የቻምፒዮንነት ክብራቸውን ካገኙ በኋላ 13 ጊዜ ይህንን ክብር ማሳካታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። ሶከር ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ሥራ ከጀመረች ጊዜ አንስቶ እስከ 2009 ድረስ ይህ ቁጥር 15 እንደነበር በወቅቱ በነበራት መረጃዎች (በተለይም ዊኪፔዲያ) ላይ ተመስርታ ክለቡ የፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን በሆነባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ስትዘግብ ቆይታለች።

ሆኖም በተለይም ከ2012 ወዲህ በሊጉ ላይ ባደረግነው የታሪክ ዳሰሳ ላይ የኢትዮጵያ ሻምፒዮናን ያሳኩ ቡድኖች ዝርዝርን ለመቃኘት ስንሞክር በበርካታ የህትመት ውጤቶች ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ያነሳቸው ዋንጫዎች 15 ሳይሆኑ 13 መሆኑን ተመዝግቦ ተመልክተናል። ዊኪፔዲያ ላይ የሰፈረውን ጨምሮ ከዚህ ቀደም በነበሩን መረጃዎች ላይ በ1983 እና የ1984 ቅዱስ ጊዮርጊስ ሻምፒዮን ስለመሆኑ የሚጠቁሙ የነበሩ ቢሆንም በእነዚህ ዓመታት ግን \”አልተካሄደም\” በሚል እንደታለፈ ለመረዳት ችለናል። ሆኖም ከሌሎች ህትመቶች ይልቅ እንደ ዋና ማስረጃ የተጠቀምነው በተለያዩ ወቅቶች የወጡ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ይፋዊ መፅሔቶች ሲሆኑ በተጨማሪም ቅዱስ ጊዮርጊስ 80ኛ ዓመት በዓሉን ባከበረበት ወቅት የታተመው ይፋዊ መፅሐፍንም እንደ ማስረጃ ተጠቅመናል።

በዚህ ፅሁፍ ላይም ለግንዛቤ ያህል ምስሎቹ የተወሰዱባቸው የህትመት ውጤቶች ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በ1993 የታተመው \”12ኛው የአፍሪካ ወጣቶች ሻምፒዮና – ልዩ እትም\” ን እና በ2004 የታተመውን \” የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዜና መፅሔት ቅፅ 1 ቁጥር 1\”  እንዲሁም በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ለ80ኛ ዓመት ክብረ በዓሉ 2008 ላይ ያሳተመው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ መፅሐፍ\” በተጨማሪም ከገለልተኛ የህትመት ውጤቶች ደግሞ በ1997 የታተመው \”የእግርኳስ ስፖርተኞች በኢትዮጵያ\” የሚለው መፅሔት ይገኙበታል።

በመሆኑም ሁለቱን የውድድር ዓመታት ሳንጨምር ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀደመው የውድድር ቅርፅ ቻምፒዮን የሆነባቸው ዓመታት 1942 ፣ 1958 ፣ 1959 ፣ 1960 ፣ 1963 ፣ 1967 ፣ 1977 ፣ 1978 ፣ 1979 ፣ 1982 ፣ 1986 ፣ 1987 እና 1988 ሲሆኑ ብዛታቸውም 13 ይሆናል። ይህንን ቁጥር ከ1990 ጀምሮ በፕሪምየር ሊግ የውድድር ቅርፅ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቻምፒዮን ከሆነባቸው 16 ዓመታት ጋር ስንደምር በአጠቃላይ የ29 ጊዜ አሸናፊ መሆኑን እንረዳለን። ይህንንም በመንተራስ ድረ ገፃችን ዓምና ቅዱስ ጊዮርጊስ ዋንጫውን ሲያነሳ 28ኛ እንዲሁም ዘንድሮ 29ኛ በማለት ስትገልፅ ቆይታለች።

በዚህ አጋጣሚ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ተቋም እነዚህና መሰል ታሪካዊ እውነታዎች በአግባቡ ተመዝግበው እንዲያልፉ ካለን ኃላፊነት በመነጨ እንጂ ሌላ ተልዕኮ የሌለው መሆኑን እየገለፅን በሀገራችን እግርኳስ ካለው ደካማ የታሪክ አመዘጋገብ አንፃር መሰል ስህተቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉም ለመጠቆም እንወዳልን። በዚህ ጉዳይ ላይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበርም ሆነ ሌላ አካል የሚሰጥ ማብራሪያን ለማስተናገድ ፣ በኛ በኩል ወይም በሌላ አካል ስህተት ካለ ሶከር ኢትዮጵያ ለመቀበልና ማስተካከያ ለማድረግ በሯ ክፍት መሆኑን እንገልፃለን።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በኮቪድ-19 ወረርሺኝ ምክንያት እንዲቋረጥ መወሰኑን ተከትሎ ከዚህ በፊት ስለተቋረጡ ውድድሮች ሶከር ኢትዮጵያ ባጠናቀረችው ታሪክ ቀመስ ፅሁፍ በ1983 በመንግሥት ለውጥ ምክንያት ፣ በ1984 ደግሞ ከሜዳ መጨቅየት ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ሻምፒዮና ሳይጠናቀቅ እና የኢትዮጵያ ሻምፒዮናም ሳይከናወን መቅረቱን በተመለከተ ከአንጋፋው ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ ጋር ያደረግናቸውን ቃለ ምልልሶች ሚያዚያ 27/2012 እና ሚያዚያ 28/2012 ለንባብ ማብቃታችን ይታወሳል። ከታች የተቀመጡትን ማስፈንጠሪያዎች በመጫንም እነዚህን ፅሁፎች በማንበብ ግንዛቤ ማግኘት እንደምትችሉ እናሳውቃለን።

ስለ 1983 ውድድር ዓመት መሰረዝ ከጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ ጋር የተደረገ ቆይታ : https://soccerethiopia.net/football/57830

ስለ 1984 ውድድር ዓመት መሰረዝ ከጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ ጋር የተደረገ ቆይታ : https://soccerethiopia.net/football/57838