አዳማ ከተማ የዲሲፕሊን ውሳኔ ተላለፈበት

አዳማ ከተማ በሁለት የቀድሞ የቡድኑ አባላት በቀረበበት አቤቱታ የዲሲፕሊን ውሳኔ ተላልፎበታል።

በኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ የሚሳተፈው አዳማ ከተማ ዓምና ግልጋሎት ከሰጡት ተጫዋቾች መካከል አማካዩ ዮሴፍ ዮሐንስ አንዱ ነው። ተጫዋቹ ዘንድሮ በድሬዳዋ ከተማ ያሳለፈ ቢሆንም አዳማ እያለ በ2013 የሐምሌ እንዲሁም በ2014 የግንቦት እና የሰኔ ወር ደሞዝ አልተከፈለኝም በማለት ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ አቤቱታ አቅርቦ ነበር።
\"\"
በጉዳዩ ዙሪያ ክለቡ ለአቤቱታው ምላሽ እንዲሰጥ ተጠይቆ ምላሽ አለመስጠቱን የገለፀው የዲሲፕሊን ኮሚቴ በ7 ቀናት ውስጥ የተጫዋቹን ደሞዝ ክለቡ እንዲከፍል አለበለዚያ ከዝውውር መስኮት እንዲታገድ ውሳኔ መወሰኑ ታውቋል።

ከክለቡ ጋር በተያያዘ ሌላ የዲሲፕሊን ውሳኔ ከ2008 እስከ ሰኔ 30/2013 የክለቡ ሀኪም በመሆን ያገለገሉት አቶ ዮሐንስ ጌታቸው የ 2011 የግንቦት እና የሰኔ (የ 2 ወር) ፣ የ 2012 የሰኔ ( የ 1 ወር) እና የፊርማ ክፍያ ( 70 ሺህ ብር ) በድምሩ የሦስት ወራት ደመወዝ እና የፊርማ ክፍያ አልተከፈለኝም በማለት ጉዳዩን ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን ኮሚቴ ወስደው ነበር።
\"\"
ጉዳዩን ከሁለቱም ወገን ሲመለከት የነበረው የዲስፕሊን ኮሚቴም አዳማ ከተማ ለ አቶ ዮሐንስ ጌታቸው የሰኔ 2012 የአንድ ወር ደመወዝ እና የፊርማ ክፍያ 70 ሺህ ብር በሚቀጥሉት ሰባት ቀናት እንዲከፍል ይህ ሳይሆን ከቀረም አዳማ ከተማ በተጫዋች ምዝገባ እና ዝውውር እንዳይስተናገድ በተጨማሪም ከፌዴሬሽኑ ጽ/ቤት ምንም ዓይነት አገልግሎት እንዳያገኝ ውሳኔ አሳልፏል።