ከ20 ዓመታት የእግርኳሱ ቆይታ በኋላ ዛሬ ጫማውን የሰቀለው ሳላዲን ሰኢድ ስለ እግርኳስ ህይወቱ ይናገራል…..

👉 \”እግርኳስ አጥንት እና ደሜ ውስጥ ነበር\”

👉 \”እኔ ሁሌም ወጣቶችን ሳገኝ የምላቸው አንድ ነገር አለ….\”

👉 \”እጅግ በጣም ብዙ ከባድ ጊዜ አሳልፌያለሁ\”

👉 \”በእግርኳስ ህይወቴ ብዙም አልጸጸትም\”

👉 \”ልጆቼም እግርኳስ ተጫዋች ቢሆኑ ደስ ይለኛል\”

የእግር ኳስ ህይወቱን ከዛሬ 20 ዓመት በፊት በሙገር ሲሚንቶ ጀምሮ በኋላም በቅዱስ ጊዮርጊስ ጎልቶ መውጣት የቻለው ሳላዲን ሰኢድ በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ከ31ዓመት በኋላ ሀገራችን ወደ አፍሪካ ዋንጫ እንድታልፍ ወርቃማዋን ጎል በማስቆጠር በብዙ ስፖርት አፍቃርያን ልብ ውስጥ መግባት ችሏል። በስድስት ዓመት የፕሮፌሽናል እግርኳስ ህይወቱም ለግብፆቹ አል-አህሊ እና ዋዲ ዳግላ በመቀጠል ወደ አውሮፓ በማቅናት ለቤልጄሙ ሊርስ ከተጫወተ በኋላ በድጋሚ ወደ አህጉራችን አፍሪካ በመመለስ ለአልጄሪያው ኤም.ሲ አልጀርስ ተጫውቶ በ2008 ወደ ቀድሞ ክለቡ በመመለስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫውቷል፡፡

በተለይ በ2009 ቡድኑ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ረጅም ጉዞ ሲያደርግ ወሳኝ ግልጋሎት ማበርከት ችሏል። በዚህም በአፍሪካ የሚጫወት ምርጥ ተጫዋቾ ሽልማት 30 እጩዎች ውስጥ መግባቱ አይዘነጋም። ሆኖም በተለያዩ የውድድር ዘመናት ጉዳት እያስተናገደ የእግርኳስ ህይወቱን ፈታኝ ሲያደርገው በመቆየቱ በአንድ ወቅት ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ እግርኳስ ለማቆም አስቦ እንደነበረ ተናግሮ ነበር። በዚህ ከባድ ጊዜ ውስጥም ሆኖ ወደ ሜዳ ተመልሶ በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ወሳኝ ጎሎችን ማስቆጠር ችሏል። ከፈረሰኞቹ ጋር ከተለያየ በኋለ እግርኳስን እስካቆመበት ጊዜ ድረስ ሲዳማ ቡና በመጫወት የእግርኳስ ህይወቱን መምራት ይታወቃል
\"\"
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድንቅ ጊዜን ያሳለፈው እና 2001፣ 2002፣ 2008 እና 2009 የሊጉን ዋንጫዎችን ያነሳው ሳላዲን በ2000 (አዲሱ ሚሊንየም) በ21ጎሎች የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ክብር ተቀዳጅቷል።

አስቀድሞ ሶከር ኢትዮጵያ የአንጋፋውን አጥቂ እራሱን ከእግርኳስ ማግለሉን በመግለፅ ከቆይታ በኋላ ከእርሱ ጋር ያደረግነውን ቃለመጠይቅ እንደምናቀርብ በገለፅነው መሰረት ከሳላዲን ሰኢድ ጋር ያደረግነው ቆይታ እንዲህ አሰናድተነዋለ።

ስላሳለፈው ረጅሙ የእግርኳስ ህይወቱ…

\”ያለፉትን ሃያ አመታት ከታዳጊ ፕሮጀክት አንስቶ ዛሬ እግርኳስ ለማቆም እስከ ወሰንኩበት ጊዜ ድረስ ባለው የእግርኳስ ህይወቴ በጣም ደስተኛ ነበርኩ። ብዙ ነገር አግኝቼበታለሁ ሀብት አፍርቼበታለው፣ ቤተሰብ፣ የሚወዱኝ የሚያከብሩኝ በርካታ ደጋፊዎችን ሌሌሎችም በርካታ ጥቅሞችን አግኝቼበታለው። በአጠቃላይ እግርኳስ ለእኔ በአጥንት እና ደሜ ውስጥ የነበረ እና ለእኔ ትልቅ ትርጉም ያለው ነገር ነበር።\”

የማትረሳው ያገባከው ጎል…

\”መቼም ብዙ አስደሳች ብዙ የሀገሬን ስፖርት አፍቃርያንን ያስፈነጠዘች ጎሎች አስቆጥሬ አውቃለው። ሆኖም ግን ግልጽ ነው። አዲስአበባ ላይ ከናይጀሪያ ጋር ስንጫወት ያስቆጠርኩት ለእኔ ምርጡ የማረሳው ጎሌ ነው። ከምንም በላይ ለእኔ ወሳኝ ነበር።\”

በእግርኳስ ሕይወቴ አላሳካሁትም ብለህ የምትጸጸትበት ነገር አለ…?

\”በእግርኳስ ህይወቴ ብዙም አልጸጸትም ፤ ይህ ነው ቀረ የምለው ነገር የለም። ሆኖም ግን ተደጋጋሚ ጉዳቶች የምፈልገው ደረጃ ላይ እንዳልደርስ አድርገውኛል ፤ እንደዛ ባይሆን ጥሩ ነበር። በተደጋጋሚ ጉዳት ምክንያት በጣም ተስፋ የሚያስቆርጡ ከባድም አስቸጋሪ የሆኑ ጊዜም አሳልፌለው። ይሄም ቢሆን ግን ደስተኛ ነኝ ፤ አልሃምዱሊላህ።\”

ጫማ የመስቀሉን ውሳኔ እንድትወስን ያደረገህ ምክንያት ምንድነው…?

\”አይ! ምንም የተለየ ነገር የለም። በቃ እኔ በዚህ ዓመት እራሴን ከእግርኳስ እንደማገል አስቤበት የወሰንከት ውሳኔ ነው። ሌላ የተለየ ምክንያት የለውም።\”

አብረውህ ከተጫወቱ አማካኞች ውስጥ ምርጡ እና አመቻችቶ አቀባዬ ነው ብለህ የምታስበው አለ…?

\”ብዙ ምርጦች ጋር ተጫውቻለሁ። ለእኔ ለሚ ኢታና በጣም ምርጡ ነበር። ረጅም ጊዜ አብረን ተጫውተናል ፤ በተለይ በኦሊምፒክ ጨዋታ ያሳለፍነው ጊዜ ምርጥ ነበር። ይህንን ነገርም ሁሌ እናገራለሁ።\”

የእግርኳስ ሕይወትህ በስኬት የተሞላ ነው እና አሁን ላለው ትውልድ ምን ትመክራለህ…?

\”እኔ ሁሌም ወጣቶችን ሳገኝ የምላቸው ምንድነው እግርኳስ ቅንነትን ነው የሚፈልገው። የቡድን አስተዳደርም ይሁን ተጫዋች በቅንነት ካልተሠራ ውጤታማ መሆን ያስቸግራል እና እኔ ማስተላለፍ የምፈልገው ያው ቅን ልቦና ካለህ የተሻለ ቦታ ትደርሳለህ። ሁሉም ተጫዋች ቅድሚያ ማሟላት ያለበት እሱን ነው።\”

ለአድናቂዎችህ እና ለአክባሪዎችህ የምታስተላልፈው መልዕክት ምንድን ነው…?

\” ከማመስገን ውጪ ምንም ማለት አይቻልም። እየደወሉልኝ ነው ያለቀሰም አለ እና ትንሽ ስሜታዊ ያደርጋል። እግርኳስ አንዳንዴ ጥሩም መጥፎም ያጋጥማል። በተለይም በመጥፎው ሰዓት ሰው ያስፈልግሃል እና እጅግ በጣም ብዙ ከባድ ጊዜ አሳልፌያለሁ በዛን ጊዜ ደጋፊዎች ከጎኔ ነበሩ። ሕይወቴ ውስጥ ትልቅ አሻራ ጥለዋል እና ስም ብጠራ ብዙ ነው። ከፕሮጀክት ጀምሮ በተለይ ጋሽ መኮንን እና ጋሽ አዳነ ለዕድገቴ ትልቅ ምክንያት ሆነውኛል። ደጋፊዎችንም ከልቤ ነው የማመሰግናቸው።\”

ከዚህ በኋላ ላለው ሕይወትህ ያለህ ዕቅድ ምንድን ነው…?

\”እውነት ከሆነ እኔ ለ ሃያ ዓመታት ከ ቢ ቡድን ጀምሮ በጣም ከባድ ነበር ፤ ዕረፍት የሌለው ማለት ነው። እግርኳስ ደግሞ ሙሉ ጊዜህን ከሰጠኸው አዕምሮህ ሊጎዳ ይችላል ፣ ልብህ ይሰበራል። በጣም ብዙ ዓይነት አሰልጣኝ ታገኛለህ እና ሁሉም ለአንተ አንድ ዓይነት ስሜት አይኖረውም። ያንን ሁሉ መስዋዕትነት ይፈልጋል እና ከባድ ረጅም ጊዜ አሳልፌያለሁ። ረጅም ዕረፍት ያስፈልገኛል። ምንም የማስብበት ሰዓት አይደለም። ጥልቅ የሆነ ዕረፍት ነው የማደርገው።\”

\"\"
የመጨረሻ ጥያቄ ላድርገውና በትዳር ሕይወትህ እንዴት ነው ስንት ልጆችን አፍርተሀል…?

\”በትዳር ከተሳሰርኩ ወደ አስር አመት ሞልቶኛል። በጣም ደስተኛ ነኝ ፤ ጥሩ ቤተሰብ አለኝ። አስቸጋሪ ጊዜ ሲያጋጥመኝ ሁሌም አብረውኝ የነበሩ እነሱ ናቸው። መጽናኛዬ እና በቅርቡ የወለድኳት አንድ ሴት ልጅ አለች ፤ እንዲሁም 4 ወንድ ልጆች በድምሩ የአምስት ልጆች አባት ነኝ።\”

ወንዶቹ ልጆችህ የአባታቸውን ፈለግ የመከተል ፍላጎት አላቸው…?

\”አዎ ይታይባቸዋል። የራሳቸውን ፍላጎት ነው የሚከተሉት እና የእነሱ ውሳኔ ነው ፍላጎታቸውን አከብራለሁ ሲጫወቱ ግን በእኔ ዘመን በነበረበት ዓይነት ሜዳ ሳይሆን የተሻለ ሜዳና ስፖርት አካዳሚ ቢፈጠርላቸው ደስ ይለኛል። ለዚህም የሚመለከተው አካልም ሆነ እኔ የተሻለ ድጋፍ ለማድረግ መሥራት አለብን ብዬ አስባለሁ። ያው ልጆቼም እግርኳስ ተጫዋች ቢሆኑ ደስ ይለኛል ፤ እኔ ብወጣም ስፖርት ስለምወድ በእነሱ ውስጥ ሆኜ አያለሁ።\”