ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሁለት ተጫዋቾቹን ውል አራዝሟል

ከቀናት በፊት የእውቅና ሽልማት ያበረከተው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የሁለት ተጫዋቾቹን ውል አድሷል።

በአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ እየተመራ ወደ ሊጉ ካደገ በኋላ በቀጣይ ዓመት ጠንካራ ቡድን ለመገንባት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ እያመጣ የሚገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአብዱለጢፍ ሙራድ እና በረከት ግዛውን ውል ለአንድ ተጨማሪ ዓመት አራዝሟል።
\"\"
በተጠናቀቀው የከፍተኛ ሊግ ውድድር ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያሳየው ወጣቱ አማካኝ በረከት ከዚህ ቀደም በጂንካ ከተማ እና ሀላባ ከተማ የተጫወተ ሲሆን ባሳለፍነው ዓመት ኢትዮጵያ መድን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ሲያድግ የነበረ ሲሆን ዘንድሮም ንግድ ባንክን ወደ ሊጉ በማሳደግ ጥሩ አበርክቶ ከነበራቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነበር። በቀጣይ ዓመትም በሊጉ ክስተት ይሆናሉ ተብለው ከሚገመቱ ተጫዋቾች አንዱ ነው።

የመስመር አጥቂው አብዱለጢፍ ሙራድ በተለያዩ ክለቦች የተጫወተ ሲሆን አብዛኛውን የእግርኳስ ህይወቱን ከአሰልጣኝ በፀሎት ጋር ሰርቷል። ከአሠልጣኙ ጋር ኢትዮጵያ መድን ወደ ሊጉ ሲያድግ ከነበሩ ተጫዋቾች መካከልም አንዱ ነበር። በዚህ ዓመትም ንግድ ባንክ ፕሪሚየር ሊጉን ሲቀላቀል ወሳኝ ሚና የነበረው አብዱልለጢፍ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ለመቆየት ተስማምቷል።
\"\"
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቀጣይ ቀናቶች የነባሮቹ ውል ማራዘምም ሆነ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ እንደሚቀላቀል ይጠበቃል።