አሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ወደ ሊጉ ሊመለስ ነው

የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና አሠልጣኝ ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሊመለስ እንደሆነ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
\"\"
በኢትዮጵያ ከፍተኛው የሊግ እርከን ውድድር ከሚሳተፉ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ወልቂጤ ከተማ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በአሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ እየተመራ 35 ነጥቦችን በመሰብሰብ 13ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል። የክለቡ አሠልጣኝ በክለቡ አለመቀጠላቸው ከታወቀ በኋላም አዲስ አሠልጣኝ ለማምጣት እንቅስቃሴ ተጀምሮ የነበረ ሲሆን ክለቡ አሁን ከአንድ አሠልጣኝ ጋር ቅድመ ስምምነት ላይ መደረሱን ድረ-ገፃችን ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
\"\"
የወልቂጤ ከተማ አሠልጣኝ ለመሆን ቅድመ ስምምነት ላይ የደረሰው ሙሉጌታ ምህረት ነው። የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ አሠልጣኝ በ2014 የውድድር ዓመት በሀዲያ ሆሳዕና ግልጋሎት ሲሰጥ የነበረ ሲሆን የአንድ ዓመት ቀሪ ውል እያለው ከክለቡ ጋር በውዝግብ መለያየቱ አይዘነጋም። አሠልጣኙም ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ ከወልቂጤ ጋር በብዙ ጉዳዮች ስምምነት ላይ የደረሰ ሲሆን አዲስ ነገር እስካልተፈጠረ ድረስ የፊታችን ሰኞ በይፋ የክለቡ አሠልጣኝ ተደርጎ እንደሚሾም አውቀናል።