አዲስ አዳጊው ሀምበሪቾ ዱራሜ ወደ ዝውውሩ ገብቷል

በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ዓመት ተሳትፎውን የሚያደርገው ሀምበሪቾ ዱራሜ የመጀመሪያ ተጫዋቹን ሲያስፈርም የሁለት ነባሮችን ውልም አድሷል።

\"\"

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2015 የውድድር ዘመን ምድብ \’ሐ\’ን በበላይነት በማጠናቀቁ በ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፎን የሚያደርገው ሀምበሪቾ ዱራሜ ከቀናት በፊት ክለቡን ያሳደጉትን አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞን ውል ማራዘሙ የሚታወስ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ ወደ ዝውውሩ በመግባት አንድ ተጫዋች ሲያስፈርም የሁለት ነባሮችን ውል ማራዘሙን ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ የደረሳት መረጃ አመላክቷል።

\"\"

የኋላሸት ፍቃዱ የክለቡ የመጀመሪያ ፈራሚ ተጫዋች ሆኗል። ከአዳማ ከተማ የተገኘውና በዲዲዬ ጎሜዝ የአሰልጣኝነት ቆይታ ወቅት በኢትዮጵያ ቡና መጫወት የቻለው አጥቂው በመቀጠል በአዳማ ከተማ እና ሀምበርቾ ዱራሜ እንዲሁም የተጠናቀቀውን ዓመት በከፍተኛ ሊጉ ገላን ከተማ ዘጠኝ ግቦችን በማስቆጠር በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ዝርዝር ውስጥ የነበረ ሲሆን ዳግም ወደ ቀድመ ክለቡ ተመልሶ ክለቡን በፕሪምየር ሊጉ ለማገልገል ፊርማውን አኑሯል።

ከአዲሱ ፈራሚ ተጫዋች በተጨማሪ ሁለት በክለቡ የነበሩ ተጫዋቾች ውላቸው ተራዝሞላቸዋል። በሀድያ ሆሳዕና ፣ ወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫውቶ ያሳለፈው አጥቂው ዳግም በቀለ ክለቡ ወደ ሊጉ ሲያድግ አስር ግቦችን በማስቆጠር የላቀ ሚና የነበረው ሲሆን በቀጣይም ዓመት ከክለቡ ጋር ለመዝለቅ በዛሬው ዕለት ውሉን አራዝሟል።

ሌላኛው ውሉን ያራዘመው ተጫዋች በአጥቂነት እና በመስመር ተከላካይነት በኢትዮጵያ መድን እና ቡራዩ ከተማ ተጫውቶ ያሳለፈው እና በተጠናቀቀው ዓመት አጋማሽ ሀምበሪቾን ተቀላቅሎ የነበረው ቶሎሳ ንጉሴ ነው። ክለቡ በቀጣዮቹ ቀናትም የአዳዲስ እና ነባር ተጫዋቾች ዝውውር እንደሚቋጭ ይጠበቃል።