የጌታነህ ከበደ ዝውውር እስካሁን መቋጫ አላገኘም

ለሲዳማ ቡና ለመጫወት ስምምነት ላይ ደርሶ የነበረው የጌታነህ ከበደ ዝውውር ሌላ መልክ መያዙ ተሰምቷል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌስቲቫል ላይ ለቀናት ቆይታ አድርጎ ከሰሞኑን ወደ ሀገር ቤት የተመለሰው አጥቂው ጌታነህ ከበደ ከተለያዩ ክለቦች ጋር ስሙ ሲየያዝ መሰንበቱ ይታወሳል። ከሳምንት በፊት ከአመሻሽ 12 እስከ ምሽቱ 4 ሰአት ድረስ ከሲዳማ ቡና አመራሮች ጋር ዘለግ ያለ ድርድ ሲያደርግ ቆይቶ ለሁለት አመት ለመጫወት ከስምምነት ደርሶ ነበር ፤ ይህንንም መረጃ በወቅቱ ማቅረባችን ይታወቃል።
\"\"
የሲዳማ ቡድን አመራሮች በንጋታው ፌዴሬሽን በመገኘት ስምምነታቸውን ለማፅደቅ ቀጠሮ ቢይዙም ይህን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ የጌታነህ ከበደ ውሉን ሊያፀድቅ አልቻለም። ሶከር ኢትዮጵያ ባደረገችው ማጣራት እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ ጌታነህ ከበደ ከወልቂጤ ከተማ ከንቲባ ጋር ከሰሞኑን መደራደሩን ለማወቅ የቻልን ቢሆም የንግራቸው መቋጫ ምን እንደደረሰ የተሟላ መረጃ አላገኘችም። በሌላ በኩል በብሔራዊ ቡድን በመካከላቸው አለመግባባት ተፈጥፎባቸው ከነበረው ከዐፄዎቹ አለቃ ውበቱ አባተ ጋር በዚህ ሳምንት መጨረሻ ተገናኝተው ጌታነህ ከበደ ወደ ክለቡ በሚቀላቀልበት ሁኔታ ዙርያ ንግግር ማድረጋቸውን አውቀናል። በአጠቃላይ ጌታነህ ከበደ የመጨረሻው ማረፊያ ባይታወቅም ሲዳማ ቡናዎች አሁንም አስቀድመው ባደረጉት ስምምነት መሰረት ውሉን ለማፀደቅ ነገ በስሙ የተዘጋጀ ማልያ በማዘጋጀት ፌዴሬሽን ቀጠሮ መያዛቸውን አውቀናል።
\"\"
ሶከር ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ ዙርያ የሚኖሩ አዳዲስ ነገሮችን ካሉ ተከታትላ የምታቀርብ መሆኑን ከወዲሁ ትገልፃለች።