በሴካፋ ከ18 ዓመት በታች ዋንጫ ዙሪያ መግለጫ ተሰጥቷል

በኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የታንዛኒያ ቆይታ ዙሪያ አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ መግለጫ ሰጥተዋል።

የሴካፋ ሴቶች ከ18 ዓመት በታች ሻምፒዮና በታንዛኒያ አስተናጋጅነት ከሐምሌ 18 ጀምሮ በአምስት ሀገራት መካከል ሲደረግ ቆይቶ ታንዛኒያን ሻምፒዮን ፣ ዩጋንዳን ሁለተኛ እንዲሁም ሀገራችን ኢትዮጵያን ደግሞ ሦስተኛ በማድረግ ተጠናቋል። በውድድሩ ላይ ሁለት ጨዋታዎችን ተረቶ በሁለቱ ድል ያስመዘገበው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ ስለ ውድድሩ እና ከጉዟቸው ጋር በተያያዘ ዛሬ ከሰዓት በፌዴሬሽኑ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በስፍራው ለተገኙ ጥቂት ጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።

\"\"

አስቀድመው አሰልጣኙ ወደ ታንዛኒያ በሰላማዊ መንገድ ጉዞ ማድረጋቸዉን ከጠቆሙ በኋላ ወደ ውድድሩ ስፍራ በመርከብ ለማቅናት መገደዳቸው በቡድኑ አባላት ላይ የጤና ዕክል እንደፈጠረ ካስረዱ በኋላ በመቀጠል ዝግጅት ሲያደርጉ የነበረው አዲስ አበባ ከመሆኑ አኳያ ታንዛኒያ ሞቃት መሆኗ እንዲሁም የልምምድ ወቅት በምሳ ሰዓት መሆኑ ፣ የውድድሩም ሰዓት በተመሳሳይ ከሰዓት መደረጉ ከፕሮግራም አወጣጥ ጋር የነበረው ሒደት ክፍተት መፍጠሩን አውስተው በእነኚህም ምክንያቶች ውጤቱ በታሰበው ልክ መሆን አለመቻሉን በንግግራቸው ጠቅሰዋል። አሰልጣኙ እንደ መልካም ተሞክሮ ብለው ካነሱት ሀሳብ መሐል የደጋፊዎች የሜዳ ላይ አደጋገፍ ሙሉ የጨዋታውን ደቂቃ ያለ ዕረፍት መሆን መቻሉ ለተጋጣሚዎቻቸው እንደጠቀማቸው ይህም እንደ ሀገርም ትምህርት ሊወሰድበት ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል።

በመቀጠል በስፍራው የተገኙ ጋዜጠኞች ጥያቄ አንስተው በአሰልጣኙ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል። በዋናነት ውድድሩ ይደረጋል የተባለበትን ቀን ታሳቢ በማድረግ ዝግጅት ጀምረው በኋላም ውድድሩ ከተቋረጠ በኋላ በድጋሚ ወደ ልምምድ መመለሳቸው ለውጤቱ ተፅዕኖ ፈጥሯል ተብለው አሰልጣኙ ተጠይቀው መቋረጡ በድንገት ስለነበር የተወሰነ የሥነ ልቦና ጉዳት እንደነበር ከገለፁ በኋላ በወቅቱ እንደ መፍቶሔ ቪዲዮ በመላላክ ተፅዕኖ እንዳይኖር ስለማድረጋቸው አሰልጣኝ እንዳልካቸው ተናግረዋል። አሰልጣኙ ለውጤቱ መጥፋት የመጀመሪያው የዩጋንዳ ጨዋታ ላይ የሰሩት ስህተት ፣ የመጀመሪያ ጨዋታዎች መደራረብ እና የአካል ብቃት ችግሮች እንደደነበሩባቸው ተጋጣሚያቸውም በዚህ ረገድ የተሻሉ መሆናቸውን አምነዋል። በመጨረሻም አሰልጣኝ እንዳልካቸው በውድድሩ ላይ የበላይነት ይዘው ለማጠናቀቅ አልመው የነበረ ቢሆንም ከዕቅዱ አንፃር ማሳካት ባለመቻላቸው የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታን ጠይቀዋል።

\"\"