​አፍሪካ | ኬንያ አዲስ አሰልጣኝ ሹማለች

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ ስድስት ከኢትዮጵያ ጋር የምትገኘው ኬንያ አዲስ አሰልጣኝ መሾሟን ዛሬ ይፋ አድርጋለች፡፡ የኬንያ እግርኳስ ፌድሬሽን በአሰልጣኝ ስታንሊ ኦኮምቢ ምትክ ቤልጂየማዊውን ፖል ፑትን የሃራምቤ ከዋክብቱ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ቀጥሯል፡፡

ከመጋቢት 2016 ጀምሮ ኬንያን በማሰልጠን ላይ የነበሩት ስታንሊ ኦኩምቢ በተለይም ከደጋፊዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ሲቀርብባቸው ነበር፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በ2016 እና 2017 መጀመሪያ ላይ በተለይ በአቋም መለኪያ ጨዋታዎች የሚያስመዘግበው ውጤት መልካም የነበረ ቢሆንም በዋና የነጥብ ውድድሮች ሽንፈትን መቅመሱ ለኬንያዊያን የሚዋጥ ጉዳይ አልሆነም፡፡ ቡድኑ በቅርብ ወራት በኢራቅ እና ታይላንድ መሸነፉም ኡኩምቢ ላይ ጫናው እንዲበረታ አድርጓል፡፡ ይህንን ተከትሎም በኒክ ሙዌንዳ የሚመራው የኬንያ እግርኳስ ፌድሬሽን አሰልጣኝ ኦኩምቢን አሰናብቶ በምትኩ ፓል ፑትን መቅጠሩን ይፋ አድርጓል፡፡

ፖል ፑት ለአፍሪካ እግርኳስ አዲስ አይደሉም፡፡ በሃገራቸው ሎክረን እና ሌረስን ያሰለጠኑት ፑት በአፍሪካ ጋምቢያ እና ቡርኪና ፋሶን መርተዋል፡፡ በተለይ በቡርኪናፋሶ አሰልጣኝነታቸው በ2013 የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያን 4-0  ማሸነፍ ችለዋል። የዮርዳኖስ ብሔራዊ ቡድንን ለጥቂት ወራት ሲያሰለጥኑ እስከቅርብ ቀናትም የአልጄሪው ሃያል ክለብ ዩኤስኤም አልጀር አሰልጣኝ ነበሩ፡፡ ዩኤስኤምን ለካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ ሲያበቁ በአልጄሪያ ሊግ ሞቢሊስ ግን ውጤት ሳይቀናቸው ሶስተኛ ደረጃን ለመያዝ ተገደዋል፡፡ በአዲሱ የውድድር ዘመንም ዩኤስኤም መልካም አጀማመር አለማሳየቱን ተከትሎ ከአልጀርሱ ክለብ የመለያየታቸው ነገር እርግጥ ነበር፡፡

ፑት የመጀመሪያ ስራቸው የሚሆነው በሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ ኬንያ ውጤታማ ማድረግ ሲሆን ለ2019 የአፍሪካ ዋንጫም ብሄራዊ ቡድን ማምራት የሚችልበትን እድል ማመቻቸትም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኬንያ ከኢትዮጵያ፣ ጋና እና ሴራ ሊዮን ጋር በምድብ 6 የምትገኝ ሲሆን በመጀመሪያ ጨዋታዋ ፍሪታውን ላይ በሴራ ሊዮን 2-1 መሸነፏ ይታወሳል፡፡ በጥቅምት 2018 በሜዳዋ ጋናን የምታስተናግድ ሲሆን በሶስተኛው የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያን ትገጥማለች፡፡ ልክእንደ ኬንያም ሁሉ ኢትዮጵያ በበኩሏ በብሄራዊ ቡድኑ መልካም ያልሆነ ውጤት ምክንያት ደጋፊዎች ደስተኛ አይደሉም፡፡ ልክ እንደኦኩምቢ ሁላ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በሰሩት ውጤታማ ያልሆነ እና ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በማያሳየው ቡድን ምክንያት ከፍተኛ ትችት ይቀርብባቸዋል፡፡   

ፎቶ: ዴቪድ ክዋሊምዋ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *