​ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና አመቱን በድል ጀምሯል

የሊጉን የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በብሔራዊ ቡድኑ የቻን ማጣርያ ሳቢያ ሳያደርግ የቀረው ኢትዮጵያ ቡና መከላከያን ገጥሞ በሳሙኤል ሳኑሚ ጎል አሸናፊ ሆኗል።

የአመቱን የመጀመሪያ ጨዋታውን በአዲሱ አሰልጣኙ ኮስታዲን ፓፒች እየተመራ የጀመረው ኢትዮጵያ ቡና ባልተለመደ መልኩ በ 4-1-3-2 ቅርፅ ወደ ሜዳ በመገባት ማናዬ ፋንቱን እና ሳሙኤል ሳኑሚን ፊት መስመር ላይ አጣምሯል። በመከላከያ በኩል የቅርፅ ለውጥ ሳይኖር ቡድኑ በተለመደው የ4-4-2 አሰላለፍ ጨዋታውን ቢጀምርም በወላይታ ድቻ ከተሸነፈበት ጨዋታ የአራት ተጨዋቾችን ቅያሪ በማድረግ ቴዎድሮስ በቀለ ፣ መስፍን ኪዳኔ ፣ ሳሙኤል ታዬ እና ተመስገን ገ/ፃዲቅን በመጀመሪያው 11 ውስጥ አካቷል።

ጨዋታው በተጀመረ ሦስት ደቂቃዎች ውስጥ መስፍን ኪዳኔ እና ኤልያስ ማሞ ከረጅም ርቀት ያደረጓቸው እና በከፍታ ወደውጪ የወጡት ሁለት ሙከራዎች ጨዋታው ከጅምሩ ብዙ ሙከራዎችን ያስተናግዳል ተብሎ እንዲጠበቅ ቢያደርግም በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ግን ተጨማሪ ሙከራዎች ሊታዩበት አልቻሉም። በሚያስገርም መልኩ በተመሳሳይ የሜዳው ክፍል ላይ አንድ ላይ ሆነው ይታዩ የነበሩት የመከላከያ የአማካይ ክፍል ተሰላፊዎች ፊት ላይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ ከነበረው ምንይሉ ወንድሙ እና ሌላኛው አጥቂ ተመስገን ገ/ፃዲቅ ጋር በአግባቡ መገናኘት ተስኗቸው ታይተዋል። የኢትዮጵያ ቡና አጥቂዎችም በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ እየሆኑ በታዩባቸው በነዚህ ደቂቃዎች ቡድኑ የወትሮውን የመስመር አጥቂዎቹን ግልጋሎት አለማግኘቱ የሜዳውን ይጎን ስፋት ለመጠቀም እንዲቸገር ሲያደርገው ተስተውሏል። ከምንይሉ ወንድሙ እና ሳሙኤል ታዬ የረጅም ርቀት ሙከራዎች ውጪ በኒዚህ ደቂቃዎች ጨዋታው ምንም ሙከራ ሳያስተናግድ ቆይቶ 35ኛው ደቂቃ ላይ በሁለቱም ቡድኖች በኩል አስገራሚ እንቅስቃሴዎችን አስተናገደ።

35ኛው ደቂቃ ላይ ምንይሉ በግራ መስመር ይዞ የገባውን ኳስ ግልፅ አቋቋም ላይ ለነበረው ሳሙኤል ታዬ ቢያቀብለውም የሳሙኤል ጠንካራ ያልሆነ ምት በሀሪሰን በቀላሉ ተያዘ። ከአንድ ደቂቃ ቆይታ በኃላም በሌላኛው የሜዳ ክፍል ሳሙኤል ሳኑሚ በግምት ከ 20 ሜትር ያደረገው ሙከራ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ወደመስመር ሲያመራ ራሱ ሳኑሚ ለማናዬ ያሻማውን ከባድ ኳስ ዐወል አብደላ ለጥቂት አወጣበት። በዚሁ ደቂቃ ላይ ምንይሉ ወንድሙ ከረጅም ርቀት ያረገውን ጠንካራ ሙከራም ሀሪሰን ሄሱ ለጥቂት ሊያድንበት ችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ በጀመረባቸው ደቂቃዎች የመከላከያ ፈጣን የማጥቃት እንቅቃሴ የታየ ሲሆን ሁለቱ የፊት አጥቂዎች ምንይሉ እና ተመስገንም ሁለት ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን አድርገው በሀሪሰን ተመልሶባቸዋል። 55ኛው ደቂቃ ላይ እያሱ ታምሩን በመጀመሪያው ግማሽ ቢጫ ካርድ በተመለከተው እና ተደጋጋሚ ጥፋት ሲፈፅም በነበረው የቀኝ መስመር ተከላካዩ አብዱሰላም ኑሩ ቀይረው ያስገቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች መጠነኛ የተጨዋቾች ሽግሽግ አድርገዋል። ጨዋታውም በሙከራ በኩል ቢዳከምም በከፍተኛ ፉክክር የቀጠለ ሲሆን 57ኛው ደቂቃ ላይ ማናዬ ፋንቱ ሳጥን ውስጥ በጥሩ አቋቅም ላይ ሆኖ ከቀኝ መስመር የተቀበለውን የነጠረ ኳስ በሚያገርም መልኩ ሲስት ከ4 ደቂቃዎች በኃላ ደግሞ ንታምቢ መሀል ሜዳ ላይ ከቅጣት ምት ሳይታሰብ የሰነጠቀው ኳስ ሳኑሚን ከ ይድነቃቸው ጋር አገናኝቶት ሳኑሚ ኳሷን በጎን ልኳታል። እነዚህ ሁለት ሙከራዎች ለቡናማዎቹ ግልፅ የማግባት አጋጣሚዎች የተፈጠሩባቸው ነበሩ።

ቴድሮስ ታፈሰን እና ሳሙኤል ሳሊሶን ቀይረው ካስገቡ በኃላ ምንይሉ ወንድሙን ብቻ ከፊት አድርገው በአምስት አማካዮች የቀጠሉት መከላከያዎች እንደ አጀማመራቸው ወደ ቡና ሳጥን ውስጥ ዘልቀው መግባት ቢቸገሩም በተለይ በግራ መስመር ባደላ ማጥቃት ክፍተቶችን ለማግኘት ሲሞክሩ ታይተዋል። ሆኖም ቡድኑ ወደ መከላከል የሚያደርገው ሽግግር ላይ በእጅጉ ክፍተት እየታየበት ለተጋጣሚው የማጥቂያ ክፍተቶችን ሲተው ታይቷል።

በዚህ መልኩ ኢትዮጵያ ቡናዎች በቀኝ መስመር በአስራት ቱንጆ አማካይነት የጀመሩት የማጥቃት እንቅስቃሴ ፍሬ ሊያፈራ ችሏል። ከ57ኛው የማናዬ ሙከራ ጋር በሚመሳሰል መልኩ እያሱ ታምሩ ከአስራት ተቀብሎ ወደመሀል የሰነጠቀው ኳስ ሳሙኤል ሳኑሚ 82ኛው ደቂቃ ላይ በምርጥ አጨራረስ  በማስቆጠር ቡናማዎቹን ባለድል ማድረግ ችሏል። ከግቡ በኃላ ኢትዮጵያ ቡና በአቡበከር ነስሩ እንዲሁም መከላከያ በምንይሉ አማካይነት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ተጨማሪ ጎሎች ሳይቆጠሩ ጨዋታው በዚሁ ተጠናቋል።

የአሰልጣኞች አስተያየት
የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ኮስታዲን ፓፒች
“እውነት ለመናገት አስቸጋሪ ጨዋታ ነበር። እንደዚህ አስቸጋሪ እንደሚሆን አልገመትኩም ነበር። ተጫዋቾቼ መሃል ሜዳ ላይ ልምምድ ላይ ከነበረን ነገር ስህተቶችን እንሰራ ነበር። ነገር ግን ፍርድ ለመስጠት ግዜው ገና ነው። ይበልጥ ተጫዋቾቻን ለመላመድ ሶስት እና አራት ጨዋታዎች ያስፈልጉናል እንዲሁም እኛ በምንፈልገው የአጨዋወት ስርዓት በዚህ ውድድር ዘመን ለመተግበር ግዜ ያስፈልገናል። በተወሰነ መልኩ ይህንን እያየን ነው። ግብ በማስቆጠራችን እድለኛ ነን። ተጋጣሚያችንም ግብ የማስቆጠር እድል ነበራችው። ሶስት ነጥብ ማግኘታችን ጥሩ ጅማሮ ነው። ዛሬ የነበረውን ረስተን ለቀጣዮ ጨዋታ ማሰብ እንጀምራለን።”

“እውነት ለመናገር ባለፎ ሳምንት ያየሁት (መከላከያ) ፈፅሞ የተለያዩ ናቸው። ሁሌም ቡድኖች ከቡና ሲጫወቱ ያላቸው ለመስጠት ነው የሚመጡት። እኛም እንዘጋጃለን። በእያንዳንዱ ጨዋታ የሚገጥመንን እናውቃለን። ዛሬ ሞክረናል ግን ነገም የተሻለ ሞክረን ደጋፊዎቻችንን ለማስደሰት እንጥራለን።”

“ለእኔ ይህ በጣም ይተለየ ነው። ደጋፊዎች ክላባቸውን የሚወዱበትን መጠን እይቼ ተገርሚያለው። በቀጣይ ጨዋታ ስታዲየሙን እንደሚሞሉት ተስፋ አለኝ።”

የመከላከያ አሰልጣኝ ምንያምር ፀጋዬ
“ሁለቱም ኳስ የሚጫወቱ ቡድኖች ናቸው። ጥሩ እንቅስቃሴ ነበር። ቡናዎችም ጥሩ ነበሩ የእኛም ቡድን ቶሎቶሎ ወደ ግብ ደርሷል። ከእረፍት በፊት የተገኙ አጋጣሚዎችን አልተጠቀምንም እነሱ ደግሞ ተጠቅመዋል።”

“መጀምሪያ ላይ ካላገባህ ኃላ ላይ እንዲህ አይነት ነገር ያጋጥማል። መጀመሪያ ላይ ምታባክናቸው ነገሮች መጨረሻ ላይ ዋጋ ያስከፍሉሃል። ባለፈው 83ኛው ደቂቃ ላይ ገብቶብናል አሁን ላይ ደግሞ እንደዚህ ነው። የትኩረት ማጣት ችግር ነው ለማለት አልችልም። ግብ ለማግባት ካላቸው ፍላጎት ነቅሎ የመሄድ ነገር ይታያል።”
“(አጨራረስ) ትልቁን ችግራችን ነው። እንደምንጫወተው እና ግብ ላይ እንደምንደርሰው አንጠቀምም። ትልቁ ችግራችን የማግባት ችግር ነው። እዚህ ላይም እየሰራን ነው።”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *