የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ ሲጀመር ባህርዳር ከተማ አሸንፏል

የ2010 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ዛሬ ክልል ላይ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲጀምር ባህርዳር ድል ቀንቶታል። ሽረ ከ መድን ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
በግዙፉ የባህርዳር ስታዲየም አክሱም ከተማን ያስተናገደው ባህር ዳር ከተማ አክሱም ከተማን 1-0 አሸንፏል። የባህርዳር ከተማ  ከንቲባ እና የአክሱም ከተማ የክለብ አመራሮች ለተጨዋቾቹ ሰላምታ ካቀረቡ በኃላ በአስደናቂ የደጋፊዎች ድባብ በተጀመረው ጨዋታ የጣና ሞገዶች የተሻለ የተንቀሳቀሱ ሲሆን በተቃራኒው አክሱሞች ተከላክለው ለመጫወት ሲሞክሩ ታይቷል።
በመጀመሪያው አጋማሽ በንፅፅር ቀዝቀዝ ያለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የታየ ሲሆን አልፎ አልፎ በሚታዩ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ከሚፈጠሩ የጎል እድሎች ውጪ እንብዛም ሳቢ የነበረ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ አልታየም።

በሁለተኛው አጋማሽ ተጠናክረው የመጡት ባህርዳር ከተማዎች ገና ጨዋታው እንደተጀመረ በ51ኛው ደቂቃ ከኢትዮጵያ ቡና በክረምቱ የተጨዋቾች የዝውውር መስኮት ወደ ባህርዳር በውሰት የተዘዋወረው ሳላምላክ ተገኝ ድንቅ ጎል ታግዘው ደጋፊዎቻቸውን አነቃቅተዋል።
ከጎሉ በኃላ ይበልጥ ተጭነው የተጫወቱት ባህርዳሮች ተጨማሪ ጎል ሊያስቆጥሩ የሚችሉበትን እድሎች ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። አክሱም ከተማዎች ጨዋታውን በአቻነት ሊያጠናቅቁ የሚችሉበትን የጠራ የግብ እድል በሙሉጌታ ብርሃነ አማካኝነት አግኝተው የግቡ ቋሚ መልሶባቸዋል። ተጋባዦቹ ከሜዳቸው ውጪ እንደመጫወታቸው የጥንቃቄ ጨዋታን መርጠው የተጫወቱ ሲሆን አልፎ አልፎ የሚያገኟቸውን የመልሶ ማጥቃት አጋጣሞዎች ለመጠቀም ሲጥሩ ተስተውሏል።

ሽረ ላይ የአምናው አስገራሚ ቡድን ሽረ እንዳስላሴ ኢትዮጵያ መድንን አስተናግዶ ጨዋታውን ያለ ግብ በአቻ ውጤት አጠናቋል። ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በታየበት ጨዋታ ባለሜዳዎቹ ሸረዎች የግብ እድል በመፍጠር ረገድ የተሻሉ እንደነበሩ ታውቋል።

ውድድሩ ነገ በሁለት ጨዋታዎች ሲቀጥል ባህርዳር ላይ አውስኮድ ከ ኢኮስኮ ፣ አአ ላይ የካ ከ ሰበታ ከተማ ይጫወታሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *