ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ በሜዳው ነጥብ ጥሏል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት በሀዋሳ የሰው ሰራሽ ሳር ሜዳ ላይ መቐለ ከተማን ያስተናገደው ሀዋሳ ከተማ ጨዋታውን ያለ ግብ አጠናቋል፡፡ ሀዋሳ በሜዳው ለመጀመርያ ጊዜ ነጥብ ሲጥል መቐለ ከተማ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ግብ ጠባቂን እንደ ተጫዋች ተጠቅሞ ጨዋታውን መጀመሩ አስገራሚ ክስተት ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ የህዝብ መዝሙር ታጅቦ በተጀመረው ጨዋታ ዐመለ ሚልኪያስ ፣ አሌክስ ተሰማ እና መድሀኔ ታደሰ የቀድሞ ክለባቸውን ለመግጠም ወደ ሜዳ ሲገቡ በግብ ጠባቂነት የምናውቀው ምህረትአብ ገ/ህይወትን ምንም እንኳን ወደ ሜዳ ባይገባም በተጫዋችነት ተጠባባቂ ወንበር ላይ አስቀምጠው ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡

ተመጣኝ ፉክክር በተስተዋለበት የመጀመርያ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል እብዛም የግብ ሙከራዎች ያልታዩበት ነበር፡፡ የመጀመሪያ የግብ አጋጣሚን ለመመልከት 20 ደቂቃ መጠበቅ ያስፈለገ ሲሆን 20ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከቀኝ መስመር አሻግሮለት አጥቂው ጋይስ አፖንግ ጥሩ ኳስ ቢያገኝም ሴላ መሀመድ ደርሶ አውጥቶበታል፡፡ መቀለዎች ተቀጣዩን ሙከራ በ33ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ምርጥ እንቅስቃሴን ሲያደርግ የነበረው አጥቂው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከመስመር ያሻገረለትን ኳስ መድሀኔ ታደሰ ከግብ ጠባቂው ሶሆሆ ሜንሳ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ቢመታም ወደ ወደ ውጭ ወታበታለች፡፡

ሀዋሳ ከተማዎች እንደቀደመው በሜዳቸው የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ባይወስዱም አልፎ አልፎ ወደ ግብ በመድረሱ ከመቐለ ከተማ የተሻሉ ነበሩ፡፡ 22ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን ከያቡን ዊሊያም ጋር በአንድ ሁለት ቅበብል ወደ ግብ በመድረስ ያሸጋረውን ኳስ ዳዊት ፍቃዱ ግልፅ የግብ እድል ቢያኝም ያመከነው ፣ 26ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ተከላካይነት የተሰለፈው አዲስአለም ተስፋዬ ወደ ሳጥን እየገፋ ገብቶ ያሳለፈለትን ኳስ ፍሬው ሰለሞን ቢያገኛትም ኢላማዋን ሳጠብቅ ወደ ውጭ የወጣችው ኳስ የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡ በ28ኛው ደቂቃ ሀዋሳ ከተማ በመስመር ፈጣን እንቅስቃሴን ሲያደርግ የነበረው ካሜሩናዊው አጥቂ ያቡን ዊሊያም ተጎድቶ መውጣቱ በተወሰነ መልኩ የነበራቸው የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ እክል ፈጥሮባቸዋል፡፡  የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 1 ደቂቃ ሲቀረው ያቡን ዊሊያምን ተክቶ የገባው ፍርዳወቅ ሲሳይ አሾልኮ ያቀበለውን ኳስ ፍሬው ሰለሞን ሞክሮ በግቡ አናት ወታበታለች፡፡

ሀዋሳ ከተማ የተሻለ እንቅስቃሴ ባሳየበት ሁለተኛ አጋማሽ እንደመጀርያው ሁሉ የሚጠቀሱ አደገኛ የግብ ሙከራዎች አልተስተናገዱም፡፡ የተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴን ከማየት ይልቅ ተጫዋቾች በግል የሚያደርጉት ያልተሳካ የግብ አጋጣሚ የመፍጠር ሒደት በሁለተኛው አጋማሽ ተስተውሏል፡፡

የሁለተኛው አጋማሽ ደቂቃዎች እየገፉ በሔዱ ቁጥር መቐለዎች በጥልቀት አፈግፍገው መጫወትን ሲመርጡ ሀዋሳ ከተማዎች አሸንፈው ለመውጣት ጫና መፍጠር ችለዋል፡፡ 90ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉአለም ረጋሳ ሁለት የመቐለ ከተማ ተጫዋቾችን አልፎ ያቀበለውን ኳስ ፍሬው ሰለሞን ከግብ ጠባቂው ፊሊፕ ኢቮኖ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ኳሷን ቢመታትም ፊሊፕ እንደምንም ያወጣበት እንዲሁም ፍርዳወቅ በመስመር በኩል ጥሩ አድርጎ ያሻገረውና አጥቂዎች ሳይደርሱበት የወጣው ኳስ ሀዋሳን የማታ ማታ ድል ልታስጨብጥ የምትችል አጋጣሚ ነበረች፡፡

ጨዋታው ያለግብ መጠናቀቁን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ በ12 ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ መቐለ ከተማ በ11 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት

ውበቱ አባተ – ሀዋሳ ከተማ

“ጨዋታውን እኛ ባሰብነው መልኩ አይደለም የተጫወትነው፡፡ ሜዳ ላይ የታየውም ከዚ በፊት ቡድናችን ላይ የተለመደው አይነት አይደለም፡፡ እንደፈለግነው ኳሱንም ፣ ጨዋታውንም ተቆጣጥረናል ማለት አልችልም፡፡ ብዙ ክፍተቶች ነበሩብን፡፡ በተለይ ኳስን ከመቆጣጠር አንፃር በጣም ክፍተቶት ነበሩ፡፡ ከእረፍት በፊት በጭራሽ ጥሩ አልነበርንም፡፡ ከዕረፍት መልስ ግን መጠነኛ መሻሻሎች ነበሩ፡፡ በአጠቃላይ እኛንም ህዝቡንም የሚመጥን ጨዋታ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ”

ዮሀንስ ሳህሌ – መቐለ ከተማ

“ተመጣጣኝ የነበረ ጨዋታ ነው፡፡ እነሱም አጥቅተዋል እኛም ፤ አጥቅተናል፡፡ እኛ ግን ሳር ላይ እንጫወታለን ብለን ነው ሰርተን የመጣነው፡፡ ሰው ሰራሽ መሆኑን ያወቅነው ዛሬ ነው፡፡ ተጫዋቾቹ ለሜዳው የሚሆን ጫማ አልነበራቸውም፡፡ በተጨማሪም ሜዳውን አንድ ቀን ብቻ ነው የሰራንበት፡፡ ሀዋሳ ነባር ቡድን ነው፡፡ እኛ አዲስ ቡድን ነን፡፡ በዛ ደረጃ ከሜዳ ውጭ ተጫውተህ ነጥብ መያዝ ትልቅ ነገር ነው፡፡ 

“እንዳያችሁት ዛሬ ግብ ጠባቂያችንን ምህረትአብ ገ/ህይወትን በተጫዋችነት በተጠባባቂ ወንበር ላይ ነበር ያደረግንው፡፡ ከጋና ያመጣነው ተጫዋች (ሚካኤል አካፉ) የሆድ ህመም ስለነበረበት 17 ሆነን ከመግባት 18 ሆኖ መገባት ይሻላል ብለን ግብ ጠባቂያችንን በተጫዋችነት እንድንጠቀም ተገደናል፡፡”

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *