ጌታነህ ከበደ ወደ ዐፄዎቹ…?

ሰሞነኛው የዝውውር መነጋገርያ ርዕስ የሆነው የጌታነህ ከበደ ቀጣይ ማረፊያው ፋሲል ከነማ ወይስ ሲዳማ ቡና?

በትናትናው ዘገባችን ጌታነህ ከበደ ስሙ ከወልቂጤ ከተማ ፣ ፋሲል ከነማ እና ሲዳማ ቡና ጋር እንደሚያያዝ እንዲሁም ከሶስቱ ክለቦች ጋር ድርድር ማድረጉን ጠቅሰን ምናልባትም ዛሬ ለሲዳማ ቡና ፊርማውን ለማዋል ቀጠሮ እንደያዘ አውስተን ነበር። ሆኖም በቀጠሮ መሠረት የሲዳማ ቡና ተወካዮች በሰዓቱ ቢገኙም ጌታነህ ከበደ ግን ሳይገኝ መቅረቱን ለማወቅ ችለናል።

በዚህ መነሻነት ትናንት ከዐፄዎቹ አለቃ ውበቱ አባተ ጋር የተገናኘው ጌታነህ ከበደ ወደ ክለቡ በሚቀላቀልበት ሁኔታ ዙርያ ንግግር ማድረጋቸውን በገለፅነው መሰረት ዛሬም ይሄ ውይይት ቀጥሎ ጌታነህን ለማስፈረም ከስምምነት መድረሳቸውን ሰምተናል።
የተለየ ነገር ካልተፈጠረ በቀር ጌታነህ ነገ ፌዴሬሽን በመገኘት ለዐፄዎቹ ውሉን ሊያስር እንደሚችል ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። ሲዳማዎችም ተጫዋቹን የግላቸው ለማድረግ አሁንም ጥረታቸውን እንደቀጠሉ ተሰምተናል።

ተለዋዋጭ በሆነው የኢትዮጵያ የዝውውር ሂደት በድርድር እና በስምምነት ብቻ ዝውውሩ ተፈፅሟል ማለት ባይቻልም አጠቃላይ በነገው ዕለት በጌታነህ ከበደ ዝውውር ዙርያ የሚኖረውን መረጃ ተከታትለን የምናቀርብ ይሆናል።