ወደ አሜሪካ ካቀናው የዋልያዎቹ ስብስብ ሁለት ሰዎች ወደ ሀገር ቤት አልተመለሱም

በአሜሪካ የስምንት ቀናት የጉብኝት የወዳጅነት ጨዋታዎችን አድርጎ ዛሬ ወደ ሀገር ቤት ከተመለሰው የዋልያዎቹ ስብስብ ሁለት ግለሰቦች አብረው እንዳልተመለሱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአሜሪካ ዋሺንግተን የጉብኝት ጨዋታዎችን አድርጎ ዛሬ ረፋድ ወደ አዲስ አበባ መመለሱ ይታወቃል። ወደ ስፍራው ካቀኑ 37 የቡድኑ አባላት መካከል አማካዩ ጋቶች ፓኖም የሙከራ ዕድል በማግኘቱ ከቡድኑ ጋር እንዳልተመለሰ ከስፍራው ሲገለፅ የነበረ ሲሆን ድረ-ገፃችን ሶከር ኢትዮጵያ አሁን በደረሳት መረጃ መሠረት ደግሞ ሁለት ሌሎች የቡድኑ አባላት ዛሬ ወደ ሀገር ቤት አልተመለሱም።

የመጀመሪያው የቡድኑ አባል ወጌሻው ሽመልስ ደሳለኝ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የትጥቅ ኃላፊው ኃይሉ አውጊቾ እንደሆኑ አረጋግጠናል።

የሁለቱ ግለሰቦች በምን ምክንያት ወደ ሀገር ቤት እንዳልተመለሱ ያልታወቀ ሲሆን ምናልባት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ነገ በሚሰጠው መግለጫ ላይ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ ለብዙሃን መገናኛ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።