አርባምንጭ ከተማ የሦስት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ ዓመቱን በተፎካካሪነት የቋጨው የአሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልዱ አርባምንጭ ከተማ ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የአምስት ነባሮችን ውልም አራዝሟል።

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ ያለፉትን ሁለት የውድድር ዘመናት በአሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ መመራት ከጀመረ ወዲህ ወደ ተፎካካሪነት መግባት የቻለው አርባምንጭ ከተማ ለቀጣዩ የሊግ ተሳፎው በተሻለ ሆኖ ለመገኘት ወደ ዝውውሩ በመግባት የሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲቋጭ የአምስት ነባሮችን ውልም አድሷል።

የክለቡ የመጀመሪያ ፈራሚዋ ግብ ጠባቂዋ ገነት ኤርሚያስ ሆናለች። በአሁኑ የአርባምንጭ አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ አማካኝነት ሀዋሳ ከተማን በመቀላቀል የክለብ ህይወትን የጀመረችው የግብ ዘቧ በመቀጠል በኢትዮ ኤሌክትሪክ የሁለት ዓመታት ቆይታን ካደረገች በኋላ ከቀድሞው አሰልጣኟ ጋር ያገናኛትን ዝውውር አጠናቃለች። ሌላኛዋ ፈራሚ አጥቂዋ ምስር ኢብራሂም ነች። ምስር በጥረት ፣ በባህርዳር ፣ ሀዋሳ እና ያለፈውን ዓመት በመቻል ቆይታ ያደረገች ሲሆን ቀጣዩ መዲረሻዋ ሀዋሳ ሆኗል። ሦስተኛዋ ፈራሚ ተከላካዩ መቅደስ ከበደ ናት አርባምንጭ ለቃ ከሀዋሳ ጋር የተጠናቀቀውን ዓመት ካሳለፈች በኋላ ደግም ወደ ቀድሞው ክለቧ ተመልሳለች።

ክለቡ ከአዳዲሶቹ ፈራሚዎች በተጨማሪ የአምስት ነባር ተጫዋቾችን ውል አድሷል። በዚህም የመስመር አጥቂዋ ትዝታ ኃይለማርያም ፣ አጥቂዋ ሰርካለም ባሳ እንዲሁም የተከላካዮቹ ከአምላክነሽ ሀንቆ ፣ ባንቺይርጋ ተስፋዬ እና ለምለም ተስፋዬን ውል ታድሷል።