ቡናማዎቹ ተከላካይ አስፈርመዋል

እስካሁን የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር ያገባደዱት ኢትዮጵያ ቡናዎች በዛሬው ዕለት ሦስተኛ አዲስ ተጫዋች ከዐየር ኃይል አስፈርመዋል።

ኒኮላ ካቫዞቪችን በአሠልጣኝነት ሾመው የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በአዳማ ከተማ እየከወኑ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች በዝውውር መስኮቱ የግብ ዘቡ አስራት ሚሻሞን ከሀምበሪቾ ዱራሜ እንዲሁም ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስን ከለገጣፎ ለገዳዲ ማስፈረማቸው ይታወቃል። ክለቡ ከሰዓት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት ደግሞ ሦስተኛ ተጫዋች ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

ክለቡን የተቀላቀለው ተጫዋች ኪያር መሐመድ ነው። ከኢትዮጵያ ቡና ከ17 ዓመት በታች ቡድን የተገኘው የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም የቅዱስ ጊዮርጊስ ከ20 ዓመት በታች ቡድን የተጫወተ ሲሆን በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ደግሞ በከፍተኛ ሊጉ ክለብ ዐየር ኃይል አሳልፎ ዳግም ወደ አሳዳጊ ክለቡ በ3 ዓመት ውል አምርቷል።