ሲዳማ ጎፈሬ ካፕ ውድድር የሚደረግበት ጊዜ ታውቋል

የሲዳማ ጎፈሬ ካፕ ውድድር የሚካሄድበት ጊዜ እና በውድድሩ የሚሳተፉ ክለቦች እነማን እንደሆኑ ይፋ ሆኗል።

የሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን ከጎፈሬ ጋር በመተባበር የሚያካሂደው የቅድመ ውድድር ዝግጅት አካል የሆነው የሲዳማ ጎፈሬ ካፕ ውድድር የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከመጀመሩ በፊት በሀዋሳ ከተማ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም እንደሚካሄድ ይፋ ሆኗል።

2013 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በድምቀት ተከናውኖ የነበረው ይህ ውድድር አሁን ሲደረግ ተሳታፊ ክለቦችን አሳድጎ እንዲሁም አዳዲስ ነገሮችን ጨምሮ እንደሚካሄድ ተጠቁሟል። ውድድሩን የማድመቅ ሥራ ዋና አዘጋጁ የሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን ከአጋሩ ጎፈሬ ጋር በመሆን ቀደም ተብሎ እየተሰራ ሲገኝ በውድድሩ የሚሳተፉ ክለቦችም ዝርዝር መለየቱን የዝግጅት ክፍላችን የደረሳት መረጃ ያመላክታል።

ከመስከረም 3 ጀምሮ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው ውድድርም ሲዳማ ቡና፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ፋሲል ከነማ፣ መቻል፣ ወልቂጤ ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ሀምበሪቾ ዱራሜ እና ሻሸመኔ ከተማ እንደሚሳተፉ ተረጋግጧል።