ሻሸመኔ ከተማ ወደ ዝግጅት የሚገባበት ቀን ታውቋል

በአሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ የሚመራው ሻሸመኔ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ነገ ይጀምራል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከ15 የውድድር ዘመናት በኋላ በቀጣዩ ዓመት ተሳትፎን የሚያደርገው አዲስ አዳጊው ሻሸመኔ ከተማ በክረምቱ የተጫዋቾች ዝውውር እንደ እዮብ ገብረማርያም ፣ ቻላቸው መንበሩ ፣ ሙሉቀን ታሪኩ ፣ ታምራት ስላስ ፣ ሔኖክ ድልቢ ፣ አሸብር ውሮ እና መስፍን ሙዜን በይፋ ያስፈረመ ሲሆን በክለቡ የነበሩ ሰባት ተጫዋቾችን ኮንትራትም ማራዘሙ ይታወሳል። በቀጣዩ ቀናትም የተጨማሪ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችን ዝውውር የሚያገባድደው ክለቡ ወደ ዝግጅት የሚገባበትን ቀን ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መረጃ አመላክቷል።

በዚህም ከነገ ዕሁድ ነሀሴ 14 ጀምሮ የክለቡ አባላት በቢሾፍቱ (ደብረዘይት) ከተማ በኳሊቲ ሆቴል መቀመጫቸው ካደረጉ በኋላ በማግስቱ ሰኞ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን እንደሚጀምሩ ታውቋል።