አዳማ ከተማ አንድ ተጫዋች ሲያስፈርም የአጥቂውን ውል አድሷል

የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ማድረግ የጀመሩት አዳማ ከተማዎች የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ሲያስፈርሙ የአጥቂያቸውን ኮንትራትም አራዝመዋል።

በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ እየተመሩ የክለቡ መቀመጫ በሆነው ከተማ ላይ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ማድረግ የጀመሩት አዳማ ከተማዎች በስብስባቸው ውስጥ ስምንተኛውን አዲስ ፈራሚ ወደ ስብስባቸው ሲያካትቱ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቹን ኮንትራት ለተጨማሪ ዓመት አራዝመዋል።

አህመድ ረሺድ የአዳማ ከተማ ስምንተኛው ፈራሚ ነው። ከደደቢት ከተገኘ በኋላ በኢትዮጵያ ቡና ፣ ድሬዳዋ ከተማ ፣ ባህርዳር ከተማ እና የተጠናቀቀውን ዓመት ደግሞ በመቻል ቆይታ የነበረው የመስመር ተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ ቀጣዩ መዳረጋቸው አዳማ ከተማ ስለመሆኑ ዝግጅት ክፍላችን ለማወቅ ችላለች።

ክለቡ የአብዲሳ ጀማልን ኮንትራትም አራዝሟል። በክለቡ ያለፉትን አራት ዓመታት ቆይታ ያደረገው አጥቂው ከክለቡ ጋር የነበረውን ሰጣ ገባ በመፍታቱ በክለቡ ለመቆየት ፊርማውን አኑሯል።