መቻል በተለያዩ ኃላፊነቶች ረዳት አሠልጣኞችን ሾሟል

ዋና አሠልጣኝ እና የቴክኒክ አማካሪ የሾሙት መቻሎች የአሠልጣኝ ቡድናቸውን በማዘመን አዳዲስ ረዳቶችን አምጥተዋል።

ከቀናት በፊት አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራን በዋና አሠልጣኝነት የሾሙት መቻሎች ጎን ለጎን የክለቡ የቴክኒክ አማካሪ በማድረግ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱን መቅጠራቸው ይታወቃል። የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በቢሾፍቱ ከተማ እየሰራ የሚገኘው ክለቡም በዛሬው ዕለት የአሠልጣኝ ቡድን አባላቱን እንደ አዲስ በማደራጀት በተለያዩ ኃላፊነቶች ለክለቡ እገዛ የሚያበረክቱ ረዳቶችን መቅጠሩን ለዝግጅት ክፍላችን ገልጿል።

ክለቡን በረዳት አሠልጣኝነት የተቀላቀለው የመጀመሪያው አሠልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ ነው። የቀድሞ የጉና ተጫዋች የነበረው ዳንኤል በስሑል ሽረ እና ደደቢት ዋና አሠልጣኝ የነበረ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንንም በምክትል አሠልጣኝነት አገልግሏል።

ሁለተኛው ምክትል አሠልጣኝ ደግሞ በለጠ ገብረኪዳን ነው። ከዚህ ቀደም በክለቡ በምክትል እንዲሁም በጊዜያዊ ዋና አሠልጣኝነት ያገለገለው በለጠ እንደ ሌላኛው ረዳት ዳንኤል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምክትልነት አሠልጥኗል።

ከሁለቱ ምክትሎች በተጨማሪ ክለቡ የሥነ-ምግብ ባለሙያ የሆነው ዳንኤል ክብረት እንዲሁም የቪዲዮ ተንታኝ የሆነው ሳላዲን መሐመድን መቅጠሩ ታውቋል።

ያለፉትን ዓመታት በግብ ጠባቂ አሠልጣኝነት በክለቡ እያገለገለ የሚገኘው በለጠ ወዳጁም ለተጨማሪ ዓመት ለመቆየት ውል ማራዘሙም ተገልጿል።