ነብሮቹ ተከላካይ አስፈርመዋል

የአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌው ሀድያ ሆሳዕና አይቮሪኮስታዊውን የመሐል ተከላካይ ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የቀጣይ ዓመት ተሳትፎአቸውን በተሻለ ተፎካካሪ ሆኖ ለመገኘት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው በመቀላቀል እንዲሁም ውላቸውን አጠናቀው የነበሩትን ኮንትራት በማራዘም የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ማድረግ ከጀመሩ ሰንበትበት ያሉት ሀድያ ሆሳዕናዎች አይቮሪኮስታዊውን የመሐል ተከላካይ ከድር ኩሊባሊን ወደ ክለባቸው መቀላቀላቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ አመላክቷል።

በተከላካይ አማካይ እንዲሁም በመሐል ተከላካይ ስፍራ ላይ መጫወት የሚችለው ተጫዋቹ የሀገሩን ክለብ ሮያል ኤፍሲን ከለቀቀ በኋላ በ2008 ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ተጫዋቹ በደደቢት መጫወት የቻለ ሲሆን ያለፉትን አምስት ዓመታት ደግሞ ከፋሲል ከነማ ጋር ቆይታን አድርጓል። ከዐፄዎቹ ጋር ረዘም ካሉ ዓመታቶች በኋላ የተለያየው ተጫዋቹ ቀጣዩ መዳረሻው ሀድያ ሆሳዕና መሆኑ ተረጋግጧል።

ከክለቡ ጋር በተያያዘ የወጣቱን የአማካይ ስፍራ ተጫዋች እንዳለ አባይነህን ውልም ለተጨማሪ አመት አድሷል።