መቻል ጋናዊ ተከላካይ አስፈርሟል

ቡድኑን በበርካታ ጉዳዮች እያጠናከረ የሚገኘው መቻል ጋናዊ የመሐል ተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

የቴክኒክ አማካሪ ከመቅጠር ጀምሮ አዳዲስ የአሠልጣኝ ቡድን አባላትን እንዲሁም ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ ያመጣው መቻል ከቀናት በፊት በቢሾፍቱ ከተማ በአሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ እየተመራ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እንደጀመረ ይታወቃል። እስካሁን አቤል ነጋሽ፣ አስቻለው ታመነ፣ ነስረዲን ኃይሉ እና ናፊያን አልዮንዚን ያስፈረመው ክለቡ አሁን ደግሞ ጋናዊውን የመሐል ተከላካይ ስቴፈን ባዱን 5ኛ ፈራሚው አድርጓል።

ስቴፈን ባዱ በሀገሩ ክለቦች ቢ ኤ ዩናይትድ፣ አዱዋና ስታርስ እና በረኩም ቼልስ የተጫወተ ሲሆን በኦማን ሊግ ለሚሳተፈው ሶሀር እንዲሁም በኩዌት ሊግ ለሚገኘው አል-ታዳሞን ግልጋሎት ሰጥቷል። ተጫዋቹ ከመቻል ጋር በበይነ-መረብ ስምምነቱን የፈፀመ ሲሆን ዛሬ ምሽት 3 ሰዓት አዲስ አበባ በመግባት በነገው ዕለት በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የአንድ ዓመት ውል ስምምነቱን የሚያፀና ይሆናል።