ጋቶች ፓኖም ዐፄዎቹን ተቀላቅሏል

ፋሲል ከነማ የአማካይ መስመር ተጫዋቹን ጋቶች ፓኖም አስፈርሟል።

ከሳምንታት በፊት ውበቱ አባተን ዋና አሠልጣኝ አድርገው የሾሙት ፋሲል ከነማዎች በዝውውር መስኮቱ ወጣት እና ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን በማስፈረም የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በሀዋሳ ከተማ እየሰሩ እንደሚገኝ ይታወቃል። በዛሬው ዕለት ደግሞ የአማካይ መስመር ተጫዋቹ ጋቶች ፓኖምን በአንድ ዓመት ውል ማስፈረማቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ያለፉትን ሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያነሳው እና ከቀናት በፊት በአሜሪካ የሙከራ ቆይታ የነበረው ጋቶች በሀገር ውስጥ በኢትዮጵያ ቡና፣ መቐለ 70 እንደርታ፣ ወላይታ ድቻ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ከሀገር ውጪ በሩሲያው አንዚ ማካቻካላ፣ በግብፅ አል ጎውና እና ሀራስ ሁዶድ እንዲሁም በሳውዲ አረቢያው አኑዋር ሳውዲ ክለብ ተጫውቶ ማሳለፉ አይዘነጋም።