ኤልያስ ማሞ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሊመለስ ነው

ኤልያስ ማሞ  ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚመለስበትን ዝውውር ለመፈፀም ከጫፍ ደርሷል።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ስማቸውን በጉልህ ከፃፉ ተጫዋቾች መካከል የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ኤልያስ ማሞ አንዱ ነው። ኤሊያስ ከቅዱስ ጊዮርጊስ መነሻውን ካደረገ በኋላ በኢትዮጵያ ቡና ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ድሬዳዋ ከተማ ፣ ጅማ አባጅፋር እና አዳማ ከተማ በፕሪምየር ሊጉ ተጫውቶ ማሳለፉ አይዘነጋም። የተጠናቀቀውን የ2015 የውድድር ዘመንን በከፍተኛ ሊጉ ሲሳተፍ በነበረው ሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን ውስጥ ቆይታውን ያደረገው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ ከዐፄዎቹ ጋር የቅድመ ውድድር ዝግጅትን በሀዋሳ ሲሰራ ሶከር ኢትዮጵያ በስፍራው ተገኝታ መታዘብ የቻለች ሲሆን ተጫዋቹም ክለቡን ለመቀላቀል ተቃርቧል።

በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሙከራ ዕድል ተሰጥቶት ከክለቡ ጋር በታደሰ እንጆሪ ሆቴል በማረፍ ልምምዱን እየሰራ የሚገኘው ተጫዋቹ በቀጣዮቹ ቀናት የሙከራ ጊዜውን እያገባደደ በመገኘቱ ክለቡን ሊቀላቀል ከጫፍ መድረሱን ሰምተናል። ተጫዋቹም በይፋ ፊርማውን ሲያኖሮ ከልብ ወዳጁ ጋቶች ፓኖም ጋር በኢትዮጵያ ቡና ከነበራቸው ቆይታ በኋላ ዳግም የሚገናኙም ይሆናል።