የዋልያዎቹ ተጋጣሚ ስብስቧን ይፋ አድርጋለች

ጳጉሜ 3 ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ያለበት የግብፅ ብሔራዊ ቡድን ለ26 ተጫዋቾች ጥሪ አቅርቧል።

በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የአህጉራችን ብሔራዊ ቡድኖች ያለፉትን ወራት በምድብ ተከፋፍለው የማጣሪያ ጨዋታዎችን ሲያደርጉ እንደነበር አይዘነጋም። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከግብፅ፣ ጊኒ እና ማላዊ ጋር ተደልድሎ የነበረ ሲሆን ወደ ዋናው ውድድር የሚያሳልፈውን ውጤት ማግኘት ሳይችል ቀርቶ ቀሪ አንድ ጨዋታ እየቀረው መውደቁን ማረጋገጡ ይታወሳል።

የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታን ከግብፅ አቻው ጋር የሚያከናውነው ብሔራዊ ቡድኑም በትናንትናው ዕለት ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ ያቀረበ ሲሆን በዛሬው ዕለት ተሰባስቦ ለጨዋታው ልምምዱ ነገ እንደሚጀምር ተገልጿል።

በመጀመሪያው ጨዋታ በኢትዮጵያ የተረታችው ግብፅ በበኩሏ ከደቂቃዎች በፊት ከኢትዮጵያ ጋር ላለባት ለምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ ለ26 ተጫዋቾች ጥሪ አስተላልፋለች። በፖርቱጋላዊው አሠልጣኝ ሮይ ቪቶሪያ የሚመራው የግብፅ ብሔራዊ ቡድን ምንም እንኳን ወደ ዋናው ውድድር የሚያልፍበትን ውጤት ቢያገኝም ለጨዋታ ከፍ ያለ ትኩረት በመስጠት ለ26 ተጫዋቾች ጥሪ አቅርበዋል።

በዚህም አምበሉ መሐመድ ሳላን ጨምሮ ሦስት ግብ ጠባቂዎች፣ ዘጠኝ ተከላካዮች፣ ሰባት አማካዮች እንዲሁም ሰባት አጥቂዎች ጥሪ ተላልፎላቸዋል። ብሔራዊ ቡድኑ ከኢትዮጵያ ጋር ከሚያደርገው ጨዋታ በተጨማሪም ከቱኒዚያ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ የሚያደርግ ይሆናል። ጳጉሜ 3 ለሚደረገው ጨዋታም ከቀጣዩ ሳምንት ሰኞ ጀምሮ ዝግጅቷን ትጀምራለች።