ክለብ አፍሪካንስ አሰልጣኙን ለማሰናበት ተቃርቧል

በጣና ሞገዶቹ ሽንፈት የገጠማቸው ክለብ አፍሪካንስ ከዋና አሰልጣኛቸው ጋር ያላቸው እህል ውሃ ሊያበቃ ተቃርቧል።

በትናንትናው ዕለት በባህር ዳር ከተማ የ2-0 ሽንፈት የገጠመው የቱኑዝያው ክለብ ዋና አሰልጣኙ ሰይድ ኤልሳይቢ ለማሰናበት ከጫፍ እንደደረሰ የተለያዩ የሀገሪቱ ሚድያዎች እየዘገቡ ይገኛሉ። Win Win የተባለው ሚድያ ከውስጥ አዋቂ አገኘሁት ብሎ እንደዘገበው ከሆነ የክለቡ ፕሬዝዳንት ዮሱፍ ኤላላሚ ከወዲሁ ከአንዳንድ አሰልጣኞች ጋር ንግግር መጀመራቸው እና የአሰልጣኙ መሰናበት አይቀሬ እንደሆነ ገልፀዋል።

በአዲሱ የውድድር ዓመት በሊጉ ካደረጉት ሦስት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ አሸንፎ በሁለቱም ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር ያልቻለው የባብ አልጃደድ ክለብ በባህር ዳር ከተማ የገጠመው የሁለት ለባዶ ሽንፈት ለአሰልጣኙ መንበር መነቃነቅ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ እየተገለፀ ይገኛል።

ከዚህ ቀደም ሴፋክስያን ፣ አል ፋታህና አል አህሊ ፕሪፖሊን ያሰለጠነው ፋትሂ ጃባል እና የቀድሞ የኤስፔራንስና ካቢልዬ አሰልጣኝ አማር አልስዋይህ የአርባ ስምንት ዓመቱን ሰይድ ኤልሳይቢን ለመተካት የታጩ አሰልጣኞች ሆነዋል።