የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ በደማቅ ሥነ-ስርዓት ነገ ይጠናቀቃል

ስምንት ክለቦች ሲያሳትፍ የቆየው የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ነገ በደማቅ ሥነ-ስርዓት ፍፃሜውን ያገኛል።


ክለቦች ከዋናው የሊግ ውድድር በፊት ራሳቸውን ይፈትሹበት ዘንድ የሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን ከጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ ብራንድ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት እና በሀዋሳ ከተማ በስምንት ክለቦች መሃል ለዘጠኝ ቀናት ሲደረግ የነበረው የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ነገ ይጠናቀቃል።

በደማቅ ስነስርዓት ይጠናቀቃል ተብሎ በሚጠበቀው የመዝጊያ ፕሮግራም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ቀደም ብሎ 8 ሰዓት ላይ ወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማ የደረጃ ጨዋታ የሚደረግበት ሲሆን 10 ሰዓት ላይ ደግሞ መቻል እና ሲዳማ ቡና የዋንጫ ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ ተገልጿል።

የዋንጫ ስነ-ስርዓቱን ለማድመቅ ጎፈሬ እና የሲዳማ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቅድመ ዝግጅታቸውን እንዳጠናቀቁ ለዝግጅት ክፍላችን ያስታወቁ ሲሆን በሀዋሳ እና በአካባቢው የሚገኙ የስፖርት ቤተሰቦችም ስታዲየም እንዲገኙ ጥሪ ቀርቧል።