ሲዳማ ቡና የውጪ ዜጋ ግብ ጠባቂ አስፈርሟል

ጋናዊው የግብ ዘብ ቀጣዩ መዳረሻው ሲዳማ ቡና ሆኗል።

በሀዋሳ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ሲያደርግ ከቆየ በኋላ በመቀጠል በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ላይም ተሳትፎን አድርጎ የነበረው ሲዳማ ቡና እስከ አሁን በዝውውር መስኮቱ በይፋ በዛብህ መለዮ ፣ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ፣ ዮሴፍ ዮሐንስ ፣ መስፍን ሙዜ ፣ ደስታ ዮሐንስ ፣ ብርሀኑ በቀለ እና ጋናዊውን ሚካኤል ኬፕሮቪን ወደ ስብስቡ የቀላቀለ ሲሆን ወጣት ተጫዋቾችንም ጭምር በሙከራ አልፎም ከታችኛው ቡድኑ ማሳደጉ ይታወሳል። አሁን ደግሞ ክለቡ ሦስተኛ የውጪ ዜጋ ተጫዋች በማድረግ ጋናዊውን ግብ ጠባቂ መሐመድ ሙንታሪን ስለ ማስፈረሙ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

የሀገሩን ክለብ አሻንቲ ኮቶኮን በመልቀቅ በ2012 ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ በጅማ አባጅፋር ፣ ሀድያ ሆሳዕና እና እንዲሁም ያለፉትን ሁለት ዓመታት ደግሞ በሀዋሳ ከተማ ቆይታ የነበረው የ31 ዓመቱ የግብ ዘብ ከሀዋሳ ጋር ያለው የውል ዘመን መጠናቀቁን ተከትሎ በይፋ ወደ ሲዳማ ቡና አምርቷል።

ክለቡ የጋናዊውን አጥቂ ፊሊፕ አጃህን ውል ለተጨማሪ ዓመት ያራዘመ ሲሆን የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታውን ኢትዮጵያ ቡናን በመግጠም በነገው ዕለት የሚጀምር ይሆናል።