የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከክላውድአውት ኩባንያ ጋር አብሮ ለመሥራት ተስማማ

“በጋራ በመሥራታችን እጅግ በጣም ዕድለኞች ነን” አቶ ባሕሩ ጥላሁን

“ለሀገራችን አሰልጣኞች እና ዳኞች የተሻለ የስልጠና ዕድል ማመቻቸት አንዱ ዓላማችን ነው” አቶ ዮሐንስ ዘውዱ


የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ እግርኳስ ለውጥ ያመጣል ብሎ የሚያምንበትን ስምምነት ዛሬ ፈጽሟል። ስፖርት ማርኬቲንግ ላይ እና አለምአቀፋዊ ግንኙነቶች ላይ እንደሚሠራ የሚታወቀው አቶ ዮሐንስ ዘውዱ እና የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ አቶ ባሕሩ ጥላሁን በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ዋና ፀሐፊው አቶ ባሕሩ “እንደ ፌዴሬሽን የሚደረገውን ለማድረግ ያህል ዓላማችን ዮሐንስ ዘውዱ ከዛሬ ጀምሮ በይፋ ኢንተርናሽናል ላይዘናቸን መሆኑን ማሳወቅ ነው።” ብለው በመግለጽ “የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የማይደርስባቸው አድማሶች አሉ። ሁሉንም ቦታ እንደርሳለን ወይም ሁሉንም የምናውቅ የተዋጣልን ነን ለማለትም አይደለም ስለዚህ አብረውን የሚሠሩ አጋሮች ያስፈልጉናል ማለት ነው። ዮሐንስ ዘውዱ በክላውድ አውት ከትላልቅ ካምፓኒዎች ጋር ያደረጋቸው ትልልቅ ግንኙነቶች አሉ። እነዚህን ካምፓኒዎች ለማግኘት እጅግ በጣም ከባድ እንደሆነ ይታወቃል። ዮሐንስ ዘውዱ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ነው ስለዚህ ለሀገሩ አስተዋጽኦ ማድረግ ይፈልጋል። አሁን ያለበት የኑሮ ሁኔታ ከእኛ የሆነ ነገር የሚፈልግበት እንዳልሆነ ይታወቃል። ስለዚህ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ዕድገት የተወሰነ ማድረግ አለብኝ ብሎ ያስባል። ጊዜውን የሚያሳልፈው ኮከብ ከሆኑ ተጫዋቾች ጋር እንደሆነ ይታወቃል እና እኛ የምንፈልገው ነገር አለ እሱም ለሀገሩ መሥራት የሚፈልገው ነገር አለ ስለዚህ አብረን መሄዱን መርጠናል። አንደኛ ውጪ ሄደው ማረፍ ከፈለጉ የሚያርፉበት እና ነጻ የሆነን ክፍያ ማመቻቸት ወይም ሊወጣ የነበረውን ገንዘብ ደግሞ በጣም ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ በኛ አስተዋጽኦ እንዲዘጋጁ ማድረግ ነው። ታዳጊዎችን ማፍራት ላይ በተመለከተ ለመጥቀስ ያህል አንዱ የክላውድ አውት ቢሮ ዱባይ ነው የሚገኘው እና ከሳውዲ አረቢያ ጋር ጠንካራ የሆነውን መንግሥታዊ ትስስር በእግርኳሱም ለማምጣት ምቹ ሁኔታ ይፈጥርልናል። ከአንድ ወር በፊት በዙም ተወያይተናል። የአልናስር  እና የሮማ የቀድሞ ሥራ አስፈጻሚ ባለፈው አዲስአበባ ነበሩ። ከክቡር ፕሬዝዳንታችን በተገኙበት ትልቅ ውይይት አድርገናል። ሰውየው የአልናስር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ከመሾማቸው ከአንድ ቀን በፊት ሳኡዲ አረቢያ ከመሄድ ነው ወደዚህ መርጠው የመጡት እና ይህም የሆነው ዮሐንስ በፈጠረው ዕድል ነው። ፍራንሲስኮ ቶቲ ፣ ባካሪ ሳኛ እና አሁን እየተጫወቱ የሚገኙትን እነ ሳካን ጨምሮ በቀላሉ የሚያገኝ ሰው ነው። ካምፓኒውም በዛ ደረጃ የሚሠራ ነው። ብዙ ውጤታማ የሆነ ሥራ እንጠብቃለን። ቢሮክራሲው እንዳያስቸግረውም የቻልነውን ሁሉ እንሞክራለን። ከካፍ እና ፊፋ ጋር ያለን ግንኙነት ብቻውን በቂ አይደለም ዮሐንስ ዘውዱ ታላላቅ የእግርኳስ ሰዎች እና ክለቦች ጋር አለም አቀፍ ሥራዎችን እንደሚሠራ ይታወቃል። ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ይዞት የመጣው ሥራ ቀላል አይደለም። ዛሬ ይፋ ሆነ እንጂ ከአንድ ወር በፊት ሾመነዋል። ልክ እንደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በመሆን ከተለያዩ የአለማችን ታላላቅ ሊጎች ጋር እና የስፖርት ትጥቅ አምራቾች ጋርም ሆነ ሌሎች ፌዴሬሽኖች ጋር በጋራ በመሆን ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በመወገን ለኢትዮጵያ እግርኳስ የሚጠቅመውን ማምጣት ነው። ብለው  ሀሳባቸውን ከሰጡ በኋላ ጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒን ለፈጠረው የግንኙነት መስመር ዕውቅና በመስጠት  በጋራ በመሥራታችን እጅግ በጣም ዕድለኞች ነን።” ብለዋል።


የካምፓኒው ተወካይ አቶ ዮሐንስ በበኩላቸው እግርኳስ ከጨዋታነቱ በዘለለ ያለውን በርካታ ፋይዳ በመግለጽ ከዚህ ቀደም ሲሠሩት የነበረው የተጫዋቾችን የዕረፍት ጊዜ እጅግ ምቹ በሆነ ሁኔታ ማዘጋጀት እንደሆነ እና እነ ሮሜሎ ሉካኩ እና ባካሪ ሳኛን የመሳሰሉ ተጫዋቾች ከዚህ ካምፓኒ ጋር እንደሚሠሩ በመጠቆም በተቋም ደረጃ ልምዱ ምን ይመስላል የሚለውን እና ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ሲመጣ የሚፈጥረውን ዕድል በማስረዳት “እኔ ሥራዬ ድልድይ ለመፍጠር ነው ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና የውጭ ሊጎች ውሰጥ ግንኙነት በመፍጠር የኢትዮጵያን እግርኳስ ፌዴሬሽን ወደ ላይ አውጥቶ ዕውቅና ለመስጠት እና በዛ ውስጥ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማድረግ ለእኛ ለሀገራችን አሰልጣኞች እና ዳኞች የማሰልጠን ዓይነት ግንኙነቶችን ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለማገናኘት እና ታዳጊዎችን የማፍራት ሥራ ከውጭ ጋር አመቻችቶ ለማሳደግ ነው። ክላውድ አውት ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሚሠራው ፌዴሬሽኑ ጉዞ በሚሄድበት ጊዜ ከሆቴሎች ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር እና ወጪውን ለመቀነስ ነው አንዱ ዓላማው” በማለትም ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።