“አሁን በጉዟችን ላይ ምንም ችግር የለም” አቶ ልዑል ፍቃዴ

ለካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ ወደ ቱኒዚያ የሚያቀኑት የጣና ሞገዶቹ ጉዞ የደረሰበትን ደረጃ የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አጋርተውናል።

“ጉዟችንን ለማደናቀፍ እየሰሩ ነው”። በማለት የባህር ዳር ከተማ ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ልዑል ፍቃዴ ወደ ቱኒዚያ ከሚያደርጉት የመልስ ጨዋታ አስቀድሞ ከጉዟቸው ጋር በተያያዘ በቱኒዚያ ኤንባሲ በኩል ቪዛዎችን ለማግኘት የተለያዩ ተግዳሮቶች ገጥሟቸው እንደነበረ እና አፋጣኝ ማስተካከያ እንዲደረግላቸው በማሰብ ከቀናት በፊት ለሶከር ኢትዮጵያ ጥሪ አቅርበው እንደነበር ይታወሳል። አሁን ደግሞ የጉዟቸው ሁኔታ አሁን ያለበትን ደረጃ አስመልክቶ ሥራ አስኪያጁ ተከታዩን ሀሳብ አጋርተውናል።

” ሰኞ በቀጠሯችን መሰረት ሄደን አንድ ሰው ብቻ ነው ነው ያለው ቪዛው አልደረሰልንም በማለት ሲመልሱን የጉዟችን ሁኔታ አሳስቦን ነበር። ሆኖም ማክሰኞ በመሄድ በተለይ የኤንባሲው ምክትል አንባሳደር የተፈጠረውን ሁኔታ ተረድተው ቁጭ ብለን ከተነጋገርን በኋላ አገልግሎቱን እንድናገኝ በማድረግ ሁሉም የልዑክ ቡድን ቪዛውን አግኝቷል። በባንክ በኩልም በተቀላጠፈ ሁኔታ የሚያስፈልገንን የውጭ ምንዛሪ አግኝተናል። ያው የዘገየ ቢሆንም አሁን በጉዟችን ላይ ምንም ችግር የለም። የተወሰነው ልዑክ ዛሬ ማምሻውን ይጓዝና የተቀረው አብዛኛው የቡድኑ አባለት ነገ ወደ ቱኒዚያ የሚያቀኑ ይሆናል። በዚህ አጋጣሚ ምክትል አንባሳደሩን እናመሰግናለን። ሁሉም የስፖርት ቤተሰብ ነው የተረባረበው እነርሱንም ማመስገን እንፈልጋለን።”