አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል

👉 “የተጠበቀው ነገር ባለመሆኑ የደገፈንን ሕዝብ ትልቅ ይቅርታ እንጠይቃለን”

👉 “ከባለፈው ስህተታችን አለመማራችን ዋጋ አስከፍሎናል”

👉 “አብዛኞቹ በልምድ ደረጃ በአፍሪካ ዋንጫ ተወዳድረው የማያውቁ ተጫዋቾች ናቸው”

👉 “በዘመናዊ እግርኳስ የሜዳ ጥቅም የሚያዝበት ምንም ምክንያት የለም ፤ ሁሉም ነገር ዕኩል ነው”

በ2024 በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ በአንደኛ ዙር ማጣሪያ ከብሩንዲ አቻቸው ጋር የተደለደሉት ሉሲዎቹ በደርሶ መልስ ውጤት 2-2 በመለያየታቸው በመለያ ምት 5ለ3 በመረታታቸው ከማጣሪያው በጊዜ ተሰናብተዋል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ደግሞ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል።

ስለ ጨዋታው…?

“ባለፈው ጨዋታም ሆነ ዛሬ አንድ አቻ ነው የወጣነው። ቀይረን መምጣት የፈለግነው ነገር በሜዳ ላይ ተሳክቷል። አሁንም ከባለፈው ስህተታችን አለመማራችን ዋጋ እንድንከፍል አድርጎናል ፤ ይህ ደግሞ በእግርኳስ የሚከሰት ነገር ነው። እነዚህ ተጫዋቾች በአብዛኛው ከ18 ዓመት በታች አምስት ተጫዋቾች አሉ ከ 20 ዓመት በታች ቡድን ነው። በልምድ ደረጃ የአፍሪካ ዋንጫ ተወዳድረው የማያውቁ ተጫዋቾች ናቸው በብዛት ያሉት ከሎዛ ፣ ከሴናፍ እና ከታሪኳ ወይም አረጋሽ በስተቀር ሌላው ተሳትፎ አያውቅም። ከ 20 በላይ ተጫዋቾች ተሳትፎ የላቸውም። ይሄን ስል ግን መሸሸጊያ መሆን የለበትም። የሜዳ ዕድል የሚባል ነገር መውሰድ አለባችሁ የሚባል ነገርም አንዳንዴ እሰማለሁ። በዘመናዊ እግርኳስ የሜዳ ጥቅም የሚያዝበት ምንም ምክንያት የለም። የጎሉ ፣ የሜዳው ፣ የኳሱ መጠን ለሁለቱም ቡድን ያገለግላል። የአየር ሁኔታው ነው እነሱም ምስራቅ አፍሪካ ናቸው ፤ የአየር ሁኔታቸው ተመሳሳይ ነው። ተመጣጣኝ ነገሮችን ከእኛ ጋር የተሳተፉበት ስላለ እንደ እግርኳስ በቀጣይ የምንማርበት ነው ብዬ አስባለሁ።”

ቡድኑ ላይ ስለታየው የአጨራረስ ድክመት…?

“ባለፈው እንደተናገርኩት ጎሎችን ለማስቆጠር እና ሀገር እና ሕዝብን ለማስደሰት ከመጠን በላይ በመጓጓት ዛሬም የተከሰተው ይህ ነው። ከዚህ በፊት ይሄ ቡድን እዚሁ ሜዳ ላይ በሁለት ጨዋታ አስር ግቦች ያስቆጠረ ፤ ከዚህ ቀደም አራት እና አምስት የሚያስቆጥር ቡድን ነው። በእነዚህ ሁለት ጨዋታዎች ግን እነዛን ዕድሎች መጠቀም አልቻለም። ትናንት ስንሠራ የነበረውን ነገር አለመሥራታችን እንደ ሀገር ዋጋ እንድንከፍል አድርጎናል። በአጠቃላይ ግን ደጋግሜ ነገሮችን ከማስቀመጥ ይልቅ የደገፈንን የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደ ሙያ ትልቅ ከበሬታ አለን። የተጠበቀው ነገር ባለመሆኑ የደገፈንን ሕዝብ ትልቅ ይቅርታ እንጠይቃለን። እነዚህ ተጫዋቾች ግን እንደ ታዳጊነታቸው በቀጣይ መማሪያ ሆኖ በዚህ የሚያቆም ስላልሆነ ነገ በተሻለ መንገድ ይደርሱበታል ብዬ አስባለሁ።”

በጨዋታው መሃል ስለሚከተሉት ተለዋዋጭ አሰላለፍ…?

“ታክቲካሊ ለውጥ ስናደርግ የነበረው ተጋጣሚ ቡድን መጀመሪያ ላይ እንደባለፈው በአንድ አጥቂ ነበር የገባው። እኛም መጀመሪያ ላይ 4-3-3 ተግብረናል። ከዛ በኋላ ግን የነሱ የመስመር ተከላካዮች የሚያገኙትን ኳስ በሙሉ ወደ እኛ ስለሚያመጡት አጥቂዎችን በማብዛት ደፍነን ለመጫወት በማጥቃት እና በመከላከል በኩል እሱን አስበን ለመተግበር ውሳኔዎች ውስጥ ገብተን ነበር። እኛ ብዙ ዕድሎችን አግኝተናል ፤ እነሱ በሁለቱም ጨዋታ ያስቆጠሩብን እኛ የምንሳሳተውን ጠብቀው እና እኛም በቀላሉ እየሰጠናቸው እንጂ እነሱ እንደ እግርኳስ ሠርተው አላስቆጠሩብንም። እንደ ቡድን ተበልጠን ቢቆጠርብን ምንም ማለት አይደለም። በሁለቱም ጨዋታ አንድ አንድ ጊዜ ብቻ መጥተው ነው ያስቆጠሩብን ፤ እኛ ከነሱ በተሻለ ብዙ ስህተቶች ነበሩብን። ያ ማለት ታዳጊ ተጫዋቾች ናቸው። ከዚህ ቀደም ረድዔት አስረሳኸኝ ግብ በማስቆጠር የምትታወቅ ናት ፤ እንደ አፍሪካም ከ 20 ዓመት በታች ከፍተኛዋ ግብ አስቆጣሪ ናት። በእግርኳስ ይፈጠራል። እንደ ቡድን ግን ሁሉም መጠየቅ አለበት ብዬ አምናለሁ።”

ካለፈው ስላልተማሩት ስህተታቸው…?

“ግብ በማስቆጠር ችግር ላይ ነው ያልተማርነው። የተሻለ ግብ ላይ ደርሰናል። ከልምድ አኳያ ወይም ከሥራ አንጻር የተሳሳትነው ነገር ካለ በደንብ እናየዋለን። ከጊዜያት በኋላ በልምድ የሚስተካከል ቡድን እንደሆነ አምናለሁ።”