ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሦስት ተጫዋቾችን የግሉ አድርጓል

የአሰልጣኝ መሠረት ማኔው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የሦስት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል።

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ ተካፋይ የሆነው እና በመድረኩም ጠንካራ ተሳትፎን በማድረግ የሚታወቀው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአሰልጣኝ መሠረት ማኔ አማካኝነት ከወራት በፊት ጀምሮ በዝውውሩ በመሳተፍ በርካታ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም እንደነበር የገለፅን ሲሆን አሁን ደግሞ የሦስት ተጨማሪ ተጫዋቾችን ዝውውር ፈፅሟል።

እፀገነት ብዙነህ ከሁለት ዓመታት በኋላ በድጋሚ ኤሌክትሪክን ተቀላቅላለች። በደደቢት ፣ አዳማ ከተማ እና በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስትጫወት የምናውቃት የመስመር ተከላካዩዋ ከሁለት ዓመታት የንግድ ባንክ ቆይታዋ በኋላ ዳግም ከአሰልጣኝ መሠረት ማኔ ጋር የተገናኘችበትን ዝውውር ቋጭታለች።

በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዲስ አበባ ተጫውታ ያሳለፈችው ንግሥት አስረስ እና በአዲስ አበባ ከተማ በመስመር አጥቂነት ስትጫወት የተመለከትናት ንግሥት ኃይሉም የኢትዮ ኤሌክትሪክ አዲሶቹ ተጫዋቾች ናቸው።