የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በነገው ዕለት ይጀመራል

የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በነገው ዕለት በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች በአዳማ ጅማሮውን ሲያደርግ የአራቱን ክለቦች የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ጥንቅር ይዘንላችሁ ቀርበናል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በ16 ክለቦች መካከል እንደሚከናወን ይታወቃል። የ2016 የሊጉ መርሐ-ግብር በነገው ዕለት መስከረም 20 ዕለተ ዕሁድ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች በይፋ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የኒቨርሲቲ ሜዳ ላይ ይጀመራል። ሶከር ኢትዮጵያም በነገው ዕለት በሚደረጉ ጨዋታዎች ዙሪያ ክለቦች ስላደረጉት የዝግጅት ምዕራፍ እና ተያያዥ ጉዳዮች የሚከተለውን ፅሁፍ አሰናድታለች።

አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

አዳማ ከተማን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያገናኘው የሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ ቀዳሚው ነው። በሊጉ ከሰባት ዓመታት በኋላ በድጋሚ የሚገናኙት ሁለቱ ቡድኖች በአንድ ከተማ ሲያደርጉ የነበረውን የዝግጅት ምዕራፍ ቋጭተው በነገው ዕለት እንደሚገናኙ ተጠብቋል። ያለፈውን የውድድር ዘመን በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ እየተመራ በዓመቱ 41 ነጥቦችን በመሰብሰብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የፈፀመው አዳማ ከተማ ያለፈው ዓመት ላይ ይታይበት ከነበረው ወጥ ያልሆነ የውድድር ጉዞው ዘንድሮ በተሻለ ቁመና ላይ ሆኖ ለመገኘት ከነሐሴ 11 ጀምሮ ለዘንድሮው የውድድር ዘመን በክለቡ መቀመጫ ከተማ ላይ ዝግጅቱን ሲያደርግ የከረመ ሲሆን ባጣቸው ወሳኝ ተጫዋቾች ምትክም ሰፋ ያሉ ዝውውሮችን ፈፅሟል። ምንም እንኳን ክለቡን በወሳኝነት ሲያገለግሉ ከነበሩት ተጫዋቾች መካከል እንደ ዳዋ ሆቴሳ ፣ ሚሊዮን ሠለሞን ፣ እዮብ ማቲዮስ እና አቡበከር ወንድሙን ለሌሎች ክለቦች አሳልፎ ቢሰጥም ወደ ዝውውሩ በመግባት ባጣቸው ምትክ ሊሆኑ የሚችሉ ወደ 12 የሚጠጉ ተጫዋቾችን በአንፃሩ ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል። ተክለማርያም ሻንቆ ፣ መላኩ ኤልያስ ፣ ጫላ በንቲ ፣ ፍቅሩ አለማየሁ ፣ ሱራፌል ዐወል ፣ ኤፍሬም ዘካሪያስ ፣ አህመድ ረሺድ ፣ ተስፋሁን ሲሳይ ፣ ሬድዋን ሸሪፍ ፣ ሀይደር ሸረፋ ፣ አሸናፊ ኤልያስ እና አቡበከር ሻሚልን ክለቡ ሲያስፈርም ከታችኛው ቡድኑም ወጣቶችን አሳድጓል። ወጣት ተጫዋቾችን በይበልጥ በመጠቀም ያለፈውን ዓመት የተመለከትናቸው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለም በዲሲፕሊን ቀጥተዋቸው የነበሩ እንደ ዊሊያም ሠለሞን እና አብዲሳ ጀማልን የመሳሰሉ ተጫዋቾችን ዳግም ወደ ስብስባቸው ሲያካትቱ በግብፅ ምድር የሙከራ ጊዜን ያሳለፈው ዮሴፍ ታረቀኝ በድጋሚ ተመልሶ ከክለቡ ጋር ይገኛል። ቡድኑ ካደረጋቸው የወዳጅነት ጨዋታዎች በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ በመሳተፍ ደካማ የምድብ ቆይታን እንዳደረገ የሚታወቅ ቢሆንም በሊጉ ላይ ግን ተለምዷዊ የወጣት ተጫዋቾችን ግልጋሎት ልምድ ካላቸው ጋር በማቀናጀት የተሻለ አቀራረብ እንደሚኖራቸው ይገመታል። ተመጣጣኝ የማሸነፍ እና የመሸነፍ ንፃሬ ውስጥ ሆኖ ያለፈውን ዓመት ያጠናቀቀው ቡድኑ ዘንድሮስ በምን አይነት መልኩ አቀራረቡን ሊያደርግ ይችላል የሚለውን ጉዳይ ነገ ንግድ ባንክን ሲገጥም የምንመለከተው ይሆናል።

በሊጉ ላይ የተሳትፎን ዕድል ከፈረሰበት 2009 በኋላ ዳግም የተጎናፀፈው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተጠናቀቀውን ዓመት በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሀ ስር ተደልድሎ ዓመቱን በበላይነት በማጠናቀቁ ነበር በፕሪምየር ሊጉ ላይ የመሳተፍ ዕድልን ያገኘው ብቅ ባለበት የሀገሪቱ ትልቁ የሊግ ዕርከን ላይ ቡድኑ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመገኘት የቅድመ ውድድር የዝግጅት ቆይታውን አዳማ ላይ ከትሞ ለወራት ሲሰራ ከርሟል። ከሌሎች ክለቦች አንፃር ቀደም በማለት ከሐምሌ 30 ጀምሮ ዝግጅቱን ሲከውን የሰነበተው ክለቡ ከታችኛው የሊግ ዕርከን ባሳደጉት አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ ፊት አውራሪነት በከፍተኛ ሊጉ የተጠቀሙባቸውን ገሚሱን ተጫዋቾችን በማቆየት ሰፋ ባለ መልኩ በዝውውር ገበያው በጥልቀት በመካፈል በርከት ያሉ ወሳኝ ተጫዋቾችን ወደ ቡድናቸው አምጥተዋል። እንደ ፍሬው ጌታሁን ፣ ሀብታሙ ሸዋለም ፣ ፈቱዲን ጀማል ፣ ፉዓድ ፈረጃ ፣ ኪቲካ ጀማ ፣ ቢኒያም ጌታቸው ፣ ሱለይማን ሀሚድ ፣ ገናናው ረጋሳ ፣ ተስፋዬ ታምራት ፣ አዲስ ግደይ እንዲሁም ሦስቱን የውጪ ዜጋ ተጫዋቾች ባሲሩ ዑመር ፣ ካሌብ አማንክዋ እና ሲሞን ፒተርን የስብስባቸው አካል አድርገው የዝግጅት ምዕራፋቸውን ሲያደርጉ ቆይተው በስተመጨረሻ ለዋናው ውድድር ዝግጁ ሆነዋል። በአዳማ የዝግጅት ቆይታቸው ወቅት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ከማድረጋቸው በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ መካፈል የቻለው ቡድኑ የምድብ ጨዋታዎችን መሻገር ባይችልም የቡድኑ የማጥቃት አቅም ግን በጊዜ ሒደት እየተዋሀደ ሲመጣ የተሻለ ቅርፅ ሊኖረው እንደሚችል ለማስተዋል ተችሏል። ቡድኑ በቅድመ ውድድር ዝግጅቱ እና በውድድሮች ወቅትም ያሳለፋቸውን ቆይታ የሚፈትሽበትን የመጀመሪያ ጨዋታው አዳማ ከተማን ነገ ከቀትር መልስ በመግጠም የሚጀምር ይሆናል።

ሲዳማ ቡና ከ ኢትዮጵያ ቡና

በፕሪምየር ሊጉ ላይ ያለፉትን ሦስት የውድድር ዘመናት በመጨረሻዎቹ የሊጉ ሳምንታት ላይ በሚያስመዘግባቸው ውጤቶች በሊጉ ላይ ሲቆይ በተደጋጋሚ የምንመለከተው ሲዳማ ቡና ካለፉት ዓመታት ትምህርት በመውሰድ ለአዲሱ የውድድር ዓመት ራሱን በምን መልኩ አዘጋጅቷል የሚለውን የምንለካበትን ቀዳሚ ጨዋታውን ነገ የሚያስመለክተን ይሆናል። የ2015 የውድድር ጊዜውን በአሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመ ቢጀምርም የኋላ ኋላ በውጤት መጥፋት የተነሳ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደን የተካው ቡድኑ አሰልጣኙን ከቀጠረ በኋላም ወጥነት የሌለውን የሊግ ቆይታን አድርጎ ዓመቱን ያጠናቀቀ ሲሆን የነበረበትን ክፍተት አርሞ ለመቅረብ በክረምቱ አለብኝ በሚላቸው ክፍተቶች ላይ ቀዳዳዎቹን መድፈን ያስቻለውን ዝውውር ፈፅሟል። ካሸነፋቸው ጨዋታዎች ይልቅ ሽንፈቱ በይበልጥ አመዝኖ 2015ን በ38 ነጥቦች 11ኛ ላይ ተቀምጠው ያጠናቀቁት ሲዳማ ቡናዎች ለ2016 ውድድራቸው ከነሀሴ 12 ጀምሮ በመቀመጫ ከተማቸው ሀዋሳ በለቀቁ ጥቂት ተጫዋቾች ምትክ ዝውውሮችን በመፈፀም እና የነባር ተጫዋቾችን ኮንትራት በማራዘም የዝግጅት ምዕራፋቸውን በወዳጅነት እንዲሁም በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ጨዋታዎች ራሳቸውን አሟሽተው የሊጉ ጉዟቸውን ‘ሀ’ ብለው ነገ ይጀምራሉ። እንደ ፍሬው ሠለሞን እና ሙሉዓለም መስፍንን አይነት ተጫዋቾች ክለቡ ቢያጣም በአንፃሩ በዛብህ መለዮ ፣ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ፣ ዮሴፍ ዮሐንስ ፣ መስፍን ሙዜ ፣ ደስታ ዮሐንስ ፣ ብርሀኑ በቀለ እና ጋናዊያኑን ሚካኤል ኬፕሮቪን እና መሐመድን ሙንታሪን የቀላቀለው ክለቡ የቅድመ ዝግጅቱ ሲሰራ ሰንብቶ አዳማ ከትሟል። በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ላይ አጀማመሩ ጥሩ ባይሆንም በሒደት ለፍፃሜ ቀርቦ በመቻል የተረታው ቡድኑ ሁለቱን የፊት መስመር ተሰላፊዎች ይገዙ ቦጋለ እና ፊሊፕ አጃህን ግልጋሎት በይበልጥ መሐል ክፍሉ ላይ ባስፈረማቸው እና ነባሮችም ጭምር አደላድሎ ስብጥሮችን ሲፈጥር በይበልጥ ያስተዋልን ሲሆን ይህንኑ የጨዋታ መንገድ በነገው የመክፈቻ ጨዋታው ላይ የሚደግም ከሆነ ከተጋጣሚው ላይ ውጤት ይዞ ሊወጣ እንደሚችል ይጠበቃል።

ሰርቪያዊውን አሰልጣኝ ኒኮላ ካቫዞቪችን በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የመጨረሻዎቹ ሳምንታት ላይ በመቅጠር በጊዜ ለዘንድሮው ዓመት ራሱን ያዘጋጀ የሚመስለው ኢትዮጵያ ቡና ለፕሪምየር ሊጉ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ከነሐሴ 5 ጀምሮ በአዳማ ከተማ ሲያደርግ ቆይቷል። ግቦችን በማስቆጠሩ ረገድ የተዋጣለት ቢሆንም ባልተናነሰ መልኩ የኋላ መስመር ተሰላፊዎቹ በሚሰሩት ስህተት በቀላሉ ግቦችን ሲያስናግድ ባለፈው ዓመት የተመለከትነው ቡድኑ የውድድር ዘመኑን በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና በመቀጠል ደግሞ በዮሴፍ ተስፋዬ ስር ካሳለፈ በኋላ በ43 ነጥቦች 4ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ መቻሉ ይታወሳል። በርከት ያሉ ነባር ተጫዋቾች ከክለቡ ጋር ኮንትራት ስላላቸው በዝውውሩ ላይ በጥቂቱ የተሳተፈው ቡድኑ በቀጥታ እና በሙከራ ምልከታ እንደ አስራት ሚሻሞ ፣ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ፣ ናሆም ጌታቸውን እንዲሁም ሁለቱን ዩጋንዳዊያን ካኮዛ ዴሪክ እና ጂኦፎሪ ዋሳዋን በማስፈረም ከነባሮቹ ጋር በማቀናጀት ልምምዳቸውን ሲሰሩ ከርመዋል። ቡድኑ በአዳማ በነበረው ዝግጅት ወቅት የወዳጅነት ጨዋታዎች ሲያደርግ ቆይቶ በመጨረሻም በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ መካፈል ችሎ ያየን ሲሆን በውድድሩም ጥሩ ተሳትፎን አድርጎ ከምድብ በማለፍ የፍፃሜ ተፈላሚ መሆኑን ያረጋገጠ  ከመሆኑ በዘለለ አዲሱ የክለቡ አለቃ ኒኮላ ካቫዞቪች በዝግጅታቸው ወቅት ቡድናቸውን የገነቡበት ሒደት በእጅጉ ጠጣር ስለመሆኑ ለማስተዋል ችለናል። በነገው ዕለት ሲዳማ ቡናን የሚያስተናግደው ክለቡ ምናልባትም በሲቲ ካፑ ውድድር ላይ ያደርገው የነበረውን እንቅስቃሴ በሊጉ ጅማሮ ላይ ካስመለከተን ረጅም ርቀትን ሊጓዝ እንደሚችል መገመት አያዳግትም።